የሲዳማ ቡናው የግብ ዘብ ዕግድ ተላልፎበታል

የሲዳማ ቡናው የግብ ዘብ ዕግድ ተላልፎበታል

ዩጋንዳዊው የሲዳማ ቡና የግብ ዘብ ኢማኑኤል ካል ከጨዋታ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የእግድ ውሳኔ ወቶበታል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው ዩጋንዳዊው የግብ ዘብ ኢማኑኤል ካልዪዋ በመጀመሪያ ዓመት የኢትዮጵያ ቆይታው ጥሩ የሚባል ጊዜን እያሳለፈ የሚገኝ ሲሆን 24ኛ ሳምንቱን ነገ በሚጀምረው ሊግም 17 ጨዋታዎች ላይ ተሳትፎ (1528 ደቂቃዎች) ለቡድኑ መልካም የሚባል ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል። በዛሬው ዕለት ከሀገረ ዩጋንዳ እየተሰሙ ባሉ መረጃዎች ደግሞ የግብ ዘቡ በጨዋታ ማጭበርበር ተጠርጥሮ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝና የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚወጣ ለጊዜው ከማንኛውም የእግርኳስ እንቅስቃሴ እንደታገደ ተጠቁሟል።

የ29 ዓመቱ የግብ ዘብ ካል ወደ ሲዳማ ከመምጣቱ በፊት በዩጋንዳ አንጋፋ በሆነው ኤክስፕረስ ክለብ የተጫወተ ሲሆን የፉፋ ኢቲክስ እና ዲሲፕሊነሪ ኮሚቴ ዲሴምበር 21 2024 ክለቡ ኤክስፕረስ ከኪታራ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ ሲመረምር ቆይቶ በዛሬው ዕለት ምርመራው የደረሰበትን ደረጃ ይፋ አድርጓል።

የዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከፊፋ ቤቲንግ ሪፖርት በደረሰው ጥቆማ ጨዋታው ለአወራራጅ ድርጅቶች ዓላማ “ተሸጧል” የሚለውን ጉዳይ እያጣራ አሁን ላይ በሂደቱ የተሳተፉ ስፖርተኞች እነማን እንደሆኑ አመላክቷል። በጊዜው ሁለቱ ቡድኖች ሲጫወቱ ኤክስፕረስ በኪታራ 7ለ0 የተረታ ሲሆን ይህም ቀድሞ የተሰራ ሴራ እንዳለና በጨዋታው ኤክስፕረስ ቢያንስ 5 ግብ ያስተናግዳል በሚል ከጨዋታው በፊት ህገወጥ ስራዎች እንደተከወኑ እየተገለፀ ይገኛል። በዚህም ሙትያባ ማይክ ጨዋታ የማጭበርበሩን ሂደት ካቴንዴ ኢቫን ከተባለ ሰው ጋር እንዳመቻቹ ተገልጿል። ከሁለቱ አካላት በተጨማሪ ደግሞ የኤክስፕረስ ክለብ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚሮ አሽራፍ በአጋርነት ስራዎችን እንደሰራ መረጃዎች መገኘቱ ተጠቅሷል። ካቴንዴ በጨዋታው ከታንዛኒያ አወራራጅ ድርጅቶች ሚሊዮኖችን (በዶላር) ቢያሸንፍም በጥርጣሬ ክፍያው እንደታገደ ተመላክቷል።

በመጀመሪያው ዙር የማጣራት ስራ በጊዜው የኤክስፕረስ ግብ ጠባቂ የነበረውና የአሁኑ የሲዳማ ቡና የግብ ዘብ ኢማኑኤል ካል እንዲሁም ምባዚራ አሽራፍ የዋና አሠልጣኙ ካዱ ባድሩን አለመኖር በተጠቀመው ሙትያባ አግባቢነት ተሳትፎ እንዳደረጉ ይፋ ሆኗል።

እጅግ በተቀናጀ ሁኔታ ምርመራውን እያደረገ የሚገኘው ፉፋ (የዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን) በይፋዊ ድህረ-ገፁ ባወጣው ዘገባ ማይክ ሙትያባ፣ አሽራፍ ሚሮ፣ አባዚራ አሽራፍ፣ ካቴንዴ ኢቫን እንዲሁም በአሁኑ ሰዓት በሲዳማ ቡና ቤት እየተጫወተ የሚገኘው ኢማኑኤል ካልዮዋ ምርመራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ የመጨረሻ ውሳኔ እስኪተላለፍ ድረስ ከማንኛውም እግርኳሳዊ እንቅስቃሴዎች እንዲታገዱ መወሰኑን አስታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ የሚወጡ አዳዲስ መረጃዎችን እየተከታተልን የምናደርስ ይሆናል።