ሪፖርት | የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ድል ቀንቷቸዋል

ሪፖርት | የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ድል ቀንቷቸዋል

ምዓም አናብስት በአራት ደቃቃ ውስጥ ባስቆጠሯቸው ሶስት ግቦች ፋሲል ከነማን ሲያሸንፉ ቢጫ ለባሾቹ በበኩላቸው ንግድ ባንክን ሁለት ለምንም ረተዋል።

ፋሲል ከነማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

የጨዋታው መጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ወገኖች በኩል ከፍተኛ የጥንቃቄ የተሞላበት የጨዋታ ስልት የታየበት ነበር። በመሀል ሜዳው የኳስ ቁጥጥር ረገድ ተመጣጣኝ ፉክክር ቢስተዋል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ደርሶ ውጤታማ ሙከራዎችን በማድረግ ረገድ ግን ደካማ ነበሩ። ጨዋታው በመሀል ሜዳው ላይ ብቻ የታጠረ በመሆኑ የመጀመሪያው አጋማሽ ያለምንም ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ስህተቶቻቸውን አርመው የገቡት መቐለ 70 እንደርታዎች በአራት ደቂቃዎች የጥቃት ማዕበል ጨዋታውን መቆጣጠር ችለዋል። በ55ኛው ደቂቃ ቦና አሊ መነሻውን ከቀኝ መስመር አድርጎ የተሻማውን እና በፋሲል ተከላካይ ተጨርፎ የደረሰውን ኳስ ግሩም በሆነ አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር መሪነቱን ሲያበስር ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ 57ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ዓለሙ እና ብርሃኑ አዳሙ በቀኝ መስመር የፈጠሩትን ቅንጅት ዳግም ቦና አሊ ለራሱና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል።

የመቐለዎች የግብ ረሃብ በዚህ ሳይገታ በ59ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ሚሊዮን ወልዴ በጥሩ ንክኪ ተቆጣጥሮ ሶስተኛውን ግብ በማስቆጠር የዐፄዎቹን ተስፋ ውሃ ቸልሶበታል። ፋሲል ከነማዎች ከደረሰባቸው ድንገተኛ ድንጋጤ በማገገም በቀኝ መስመር በኩል አዘንብለው በማጥቃት ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረቶችን ቢያደርጉም የአናብስቱን ጠንካራ የመከላከል አጥር ሰብረው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው በ3-0 ውጤት ተጠናቋል።

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በእንቅስቃሴ ረገድ ቀዝቃዛ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ ወልዋሎዎች በቆሙ ኳሶች ላይ በነበራቸው ብልጫ ተደጋጋሚ ስጋቶችን መፍጠር የቻሉ ሲሆን በ15ኛው ደቂቃ ኮንኮኒ ሀፊዝ ለጥቂት የወጣች የግንባር ኳስ ሙከራ ቢያደርግም በ38ኛው ደቂቃ ግን ነጻነት ገብረመድን ከቅጣት ምት የተሻገረ እና በኮንኮኒ ሀፊዝ እና ጌትነት ተስፋዬ የተመቻቸለትን የግንባር ኳስ በመቀስ ምት (Bicycle Kick) ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።

ከእረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች ጨዋታውን ለማሸነፍ በነበራቸው ከፍተኛ የማጥቃት ተነሳሽነት፣ ሜዳው ላይ እጅግ ፈጣን የሆኑ ሽግግሮችን መመልከት ተችሏል። በተለይም ኳስን ከራስ ክልል በፍጥነት በማውጣት በሁለቱም የግብ ክልሎች ላይ በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉ ቢሆንም ይህ ፍጥነት ግን ወደ ረባ የግብ ሙከራ ሳይቀየር ቀርቷል ይልቁንም አጋማሹ በአላስፈላጊ ንክኪዎችና ጥፋቶች ምክንያት ጨዋታው በዳኛ ፊሽካ በተደጋጋሚ በመቋረጡ የሁለቱን ክለቦች የሽግግር ሂደት ሳቢነት አሳጥቶታል።

የመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ (90+3) ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጫዋቾች በፈጠሩት የመግባባት ስህተት ሳቢያ ተቀይሮ የገባው ናሆም ኃይለማርያም ስህተቱን ተጠቅሞ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቢመልሰውም የተመለሰውን ኳስ በቅርብ ርቀት ያገኘው ፍሬው ሰለሞን በተረጋጋ መንፈስ መረቡ ላይ በማሳረፍ የቡድኑን ወሳኝ ድል አረጋግጧል። ይሄንንም ተከትሎ ጨዋታው በወልዋሎ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።