ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ28ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ28ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

28ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል፤ ጨዋታዎቹ የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ፋሲል ከነማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

በአርባ ሁለት ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ሰሞነኛ ጥሩ ብቃታቸውን በማስቀጠል ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።

አራት ተከታታይ ሽንፈቶች በማስመዝገብ ጭምር ካሳለፏቸው ሰባት አስከፊ ድል አልባ ሳምንታት በኋላ በመደዳ ሁለት ጨዋታዎች አሸንፈው የሊጉን መሪ እየተከተሉ የሚገኙ ክለቦችን የተቀላቀሉት አፄዎቹ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድሎች ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ። ወደ ድል በተመለሰባቸው መርሐ ግብሮች የተሻሻላ ብቃት ያሳየው ቡድኑ በያዘው የአሸናፊነት መንገድ ለመዝለቅ ባለፉት አራት ጨዋታዎች መረቡን ያላስደፈረው የተከላካይ ክፍል ጥንካሬ ማስቀጠል እንዲሁም የፊት መስመሩን ይበልጥ ማጠናከር ይኖርበታል።

በሀያ ስድስት ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቐለ 70 እንደርታዎች ወደ ወራጅ ቀጠናው መውጫ በር ለመጠጋት የሚያስችላቸውን ድል ፍለጋ ከአፄዎቹ ጋር ይፋለማሉ።

በመጨረሻው ሳምንት ወልዋሎን ሁለት ለ አንድ በማሸነፍ የስድስት ሳምንታት ድል አልባ ጉዟቸውን የገቱት ምዓም አናብስት የዛሬው ጨዋታ ከወራጅ ቀጠናው የሚወጡበትን ዕድል ለማለምለም የሚያደርጉት እንደመሆኑ ወሳኝነቱ ትልቅ ነው። ተጋጣሚያቸው ተከታታይ ድሎች አስመዝግቦ በጥሩ የአሸናፊነት መንፈስ የሚገኝ ከመሆኑ አንፃርም ለፍልሚያው በሚመጥን አኳኋን መቅረብ ይጠበቅባቸዋል። በተለይም በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸው በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ካላስተናገደው የዐፄዎቹ የኋላ ክፍል ለሚጠብቀው ፈተና መዘጋጀት ይኖርበታል።

ፋሲል ከነማዎች አምሳሉ ጥላሁንን በጉዳት ሞየስ ፖዋቲን በ5 ቢጫ ካርድ ምክንያት በቅጣት ዛሬ አያገኙም። መቐለ 70 እንደርታዎች ባለፉት ጨዋታዎች ካልተሰለፈው አሸናፊ ሀፍቱ በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ ቀይ ካርድ የተመለከተው አብዱለጢፍ ባምባ እና አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በቅጣት ምክንያት አያሰልፉም።

ሁለቱም ቡድኖች የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ 7 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም በተመሳሳይ አንድ አንድ ጨዋታ ላይ ድል አድርገው በተቀሩት 5 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ሁለቱም ቡድኖች በእኩሌታ አራት አራት ግቦች አስቆጥረዋል።

ወልዋሎ ዓ/ዩ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በሀያ ዘጠኝ ነጥብ 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ወልዋሎዎች ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።

ቢጫዎቹ ሽንፈት ባልቀመሱባቸው ሰባት ጨዋታዎች ሦስት ድሎች እና አራት የአቻ ውጤቶች በማስመዝገብ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ቢችሉም በመደዳ በገጠሟቸው ሁለት ሽንፈቶች ዳግም ወደ አደገኛው ቀጠና እንዲመለሱ ሆኗል። ጠንካራ ቡድኖች በገጠመባቸው ጨዋታዎች ላይ በብዙ ረገድ የተሻሻለ እንቅስቃሴ በማሳየት ደረጃውን ማሻሻል ችሎ የነበረው ቡድኑ ዳግም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚያደርገው ፍልሚያ በተለይም በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች የተስተዋሉበትን የትኩረት ማነስ ችግሮችን መቅረፍ ግድ ይለዋል። በወላይታ ድቻ እንዲሁም በመቐለ 70 እንደርታ ሽንፈት ባስተናገደባቸው መርሐ ግብሮች ላይ በመጨረሻው እና በመጀመሪያው ደቂቃ ላይ ግቦች ያስተናገደው ቡድኑ ጠንካራ የፊት መስመር ያለውን ቡድን በሚገጥምበት የዛሬው ጨዋታ በቀዳሚነት ባለፉት ጨዋታዎች የተስተዋሉበትን የመከላከል ችግሮች ማረም ይኖርበታል።

በሰላሣ አራት ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመጨረሻው ሳምንት በሊጉ መሪ ከገጠማቸው ሽንፈት ለማንሰራራት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ።

ከ23ኛ እስከ 26ኛ ሳምንት በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው አስራ ሁለት ነጥቦች አስሩን በማሳካት አስደናቂ ጊዜ ያሳለፉት ሀምራዊ ለባሾቹ ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ብለው ለመቀመጥ እና ከስጋት ከቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ ዳግም ወደ ድል መመለስ ይኖርባቸዋል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ከዚህ ቀደም የቡድኑ ዋነኛ ድክመት የነበረውና በቅርብ ጨዋታዎች ውስን መሻሻል ያሳየው የተከላካይ ክፍሉን ለውጥ ማስቀጠል እንዲሁም በሊጉ ከመቻል ጋር በጣምራ ከፍተኛ የግብ መጠን በማስቆጠር ቀዳሚ የሆነውን የማጥቃት ጥምረቱ ውጤታማነት ማስቀጠል ይኖርበታል።

ወልዋሎዎች ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስብ ይዘው ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ግብ ጠባቂው ጊቢ ጆቤ እና ተስፋዬ ታምራት በቅጣት ምክንያት ቡድናቸውን አያገለግሉም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 3 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም በእኩሌታ አንድ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ሲችሉ በአንዱ ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በግንኙነታቸውም 10 ጎሎች የተቆጠሩ ሲሆን ሁለቱም በተመሳሳይ 5 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።