ሪፖርት| መቻል ተከታታይ ድል ሲያሳካ ሀዋሳ ከተማና ሽረ ምድረ ገነት ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት| መቻል ተከታታይ ድል ሲያሳካ ሀዋሳ ከተማና ሽረ ምድረ ገነት ነጥብ ተጋርተዋል


በ27ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ሳቢ ያልነበረው የሀዋሳ ከተማና ምድረ ገነት ሽረ ጨዋታ ያለ ግብ ሲጠናቀቅ በምሽቱ ሳቢ ጨዋታ መቻል ከመመራት ተነስቶ ድሬዳዋ ከተማን አሸንፏል

ሀዋሳ ከተማ ከ ሽረ ምድረገነት

ከትናንት በስቲያ ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት በዝናብ ምክንያት ለዛሬ የተሸጋገረው ጨዋታ ለተመልካች ሳቢ አልነበረም። በጨዋታው ሽረ ምድረገነቶች ሁለተኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ ስንታየሁ ወለጬ ከረጅም ርቀት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ አውጥቶበታል።

ሀዋሳዎች በጨዋታው የተሻለውን ሙከራቸውን 45+1ኛው ደቂቃ ላይ አድርገው ተባረክ ሄፋሞ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ሽረዎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ፈጣን አጀማመር አድርገው በኃይሉ ግርማ ከቅጣት ምት ያደረገውን ድንቅ ሙከራ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ አስወጥቶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ይህ ነው የሚባል ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይፈጠር ጨዋታው 0-0 ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ መቻል

ማራኪ ፉክክር በተደረገበት የምሽቱ ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ ገና በ6ኛው ደቂቃ ነበር ጨዋታውን መምራት የጀመሩት። ጀሚል ያዕቆብ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው መሐመድኑር ናስር ኳሱን ግብ አድርጎታል።

መቻሎችም ፈጣን ምላሽ በመስጠት 15ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ዓለምብርሃን ይግዛው ከረጅም ርቀት እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የመታው ኳስ ፍሬው ጌታሁንን አልፎ መረብ ላይ አርፏል።

መቻሎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት የሚችሉበት አጋጣሚ  አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ሳጥን ውስጥ ኮሊንስ ኮፊ ላይ በተሠራ ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አብዱልከሪም ወርቁ መትቶት ፍሬው ጌታሁን አድኖበታል።

ይህን ዕድል ያልተጠቀመው አብዱልከሪም ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ግን ድንቅ ኳስ አመቻችቶ ለኮሊንስ ኮፊ አቀብሎት አጥቂው በተረጋጋ አጨራረስ ቦታ ዐይቶ ኳሱን አስቆጥሮ መቻልን ወደ መሪነት መልሷል።

ከዕረፍት መልስ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ሁለቱም ቡድኖች ተዳክመው ሲቀጥሉ በመቻል በኩል በረከት ደስታ 65ኛው ደቂቃ ላይ ወርቃማ ዕድል ሲያባክን 81ኛው ደቂቃ ላይ ግን ከሳጥን ውጪ ድንቅ ሙከራ አድርጎ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሴኮንዶች ቀርተው 90+7′ ላይ ድሬዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ወርቃማ ዕድል አግኝተው መሐመድኑር ናስር ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል። ይህም ለብርቱካናማዎቹ እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። ጨዋታውም በመቻል 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።