የጣና ሞገዶቹ በአደም አባስ የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ከኢትዮጵያ መድን ጋር 1-1 ተለያዩ

በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ባስመለከተን የመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኖቹ በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ ባመዘነ አጨዋወት የተንቀሳቀሱበት ሲሆን ሁለቱም በተመሳሳይ
ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ደርሶ ጥቃት በመሰንዘር ረገድ ድክመቶች ታይቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ መድኑ አማኑኤል ኤርቦ 32ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ የመቀስ ምት አስደናቂ ሙከራ ካደረገ በኋላም 41ኛው ደቂቃ ቡድኑን መሪ ያደረገች ግብ ማስቆጠር ችሏል። አጥቂው በመልሶ ማጥቃት የተገኘው እና ብሩክ ሙሉጌታ ያቀበለውን ኳስ ግብ ጠባቂውን በማለፍ በጥሩ አጨራረስ ግብ አስቆጥሮ የኢትዮጵያ መድንን መሪ ማድረግ ችሏል።

በሁለተኛው አጋማሽ ባህር ከተማዎች ብልጫ ወስደው የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫናዎችን ፈጥረው መጫወት የቻሉ ሲሆን 82 ኛው ደቂቃ ላይ በአንተነህ ተፈራ እንዲሁም በወንድሰን በለጠ የግንባር ኳስ አማካኝነት የተሞከረው ሙከራ እንደምንም ብለው ተከላካዮችና የግቡ አግዳሚ ተረባርበው መልሰውታል።
በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች እጅግ ጫና ፈጥረው መጫወታቸውን የቀጠሉት የጣና ሞገዶቹ መደበኛው የጨዋታ ሰዓት እና የጭማሪ ደቂቃዎች ተጠናቀው የዳኛ ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት 90+6 ላይ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ተቀይሮ የገባው አደም አባስ ከተከላካዮች ተሻግሮ በግንባር የተጨረፈውን ኳስ አግኝቶ በጥሩ ቅልጥፍና ተከላካዮችን አልፎ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም የጣና ሞገዶቹ የማታ ማታ ነጥብ ተጋርተው እንዲወጡ አስችላ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

