“ጋሞ ጨንቻን እንደ አንዱ ልጄ ነው የምቆጥረው”
“ተጫዋቾቼ በስነ-ምግባራቸው እና በአንድነታቸው እጅግ የሚያስቀኑ ናቸው”
“ያለን ጥሩ የሆነ የቡድን መንፈስ እና ተግቶ መስራታችን ለዚህ ውጤት አብቅቶናል”

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 2018 ውድድር ዓመት በምድብ “ሀ” ተደልድሎ ውድድሩን ሲያካሂድ የነበረው ጋሞ ጨንቻ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆኑ ይታወሳል፤ የቡድኑ መስራች ዋና አሰልጣኝ ማቴዎስ ለማ ይህንን ታሪካዊ ስኬት አስመልክቶ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረገው ቆይታም እንደሚከተለው አቅርበናል።
የውድድር ዓመቱ ጉዞ እና የነበሩ ፈተናዎች ምን ይመስላሉ
የውድድር ዓመቱ በተለያዩ ክለቦች መካከል ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ነበረ። በስተመጨረሻ በእኛ የበላይነት በመጠናቀቁም ደስ ብሎኛል። በውድድር ዓመቱ የነበሩ የጨዋታ መደራረቦች እንዲሁም ውድድሩን በአንድ ቦታ ለረጅም ጊዜያት መካሄዱ በተጫዋቾች ላይ የመሰላቸት ስሜት ፈጥሮብን ነበር እና ይሄ ቆይታችንን ከባድ አድርጎብን ነበር።
ጋሞ ጨንቻን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳደግህ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ
ጋሞ ጨንቻን ወደ ፕሪምየር ሊግ ማሳደግ መቻላችን በህይወቴ ትልቁ ደስታዬ ነው። ቡድኑን ከተቀላቀልኩ ጀምሮ ላለፉት ሶስት ዓመታት አብረን የቆየን ሲሆን ውጤቱም ልክ እንደ ልጅ መውለድ አይነት ልዩ ስሜት ነው የፈጠረብኝ። ጋሞ ጨንቻን ሁሌም እንደ አንዱ ልጄ ነው የምቆጥረው።
ጋሞ ጨንቻ በውድድር ዓመቱ ላስመዘገበው ታሪካዊ ስኬት ዋነኛ ጠንካራ ጎኑ ምን ነበር
ቡድናችን እጅግ ጠንካራና ድንቅ ተጫዋቾች አሉት። በተለይም በሜዳ ላይ ያላቸው ስነስርአት፣ ታዛዥነት እና እርስ በእርስ ያላቸው ፍቅር እጅግ የሚያስቀና ነው። በውድድሩ ወቅት ከሁሉም ክለቦች ያነሰ የካርድ ብዛት የታየብን ለስፖርታዊ ጨዋነት ቅድሚያ በመስጠታችን ነው። ይሄም ውጤታማ እንድንሆን ረድቶናል።
በተጨማሪም ተግቶ መስራታችን የፈለግነውን ውጤት እንድናመጣ አስችሎናል። ለዚህ ውጤት መሳካት ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ከጎናችን ለነበሩት ለጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ለዶ/ር ደምስ አድማሱ ፣ ለቤተሰቦቼ ፣ ለተጫዋቾቼ እና ለደጋፊዎቻችን ምስጋናዬ የላቀ ነው።

