ሪፖርት| ፈረሰኞቹ ዳግም ወደ ድል ተመልሰዋል

ሪፖርት| ፈረሰኞቹ ዳግም ወደ ድል ተመልሰዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ በፍፁም ጥላሁን ብቸኛ ግብ አዳማ ከተማን በመርታት ደረጃውን አሻሻለ።

በደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ ታጅቦ የተካሄደው የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ መርሐ ግብር በሙከራዎች ያልታጀበ እና የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ከተደረገው ፉክክር ውጭ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየበት ነበር። አጋማሹም ፀጋ ከድር በረዥሙ አሻግሮት ግብ ጠባቂው አላዛር ማርቆስ ከግብ ክልሉ ወጥቶ በግምባሩ ካወጣው እና አቡበከር ሳኒ ከቀኝ መስመር አሻምቶት ቢንያም አይተይ በግምባሩ ካደረገው ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ አልተደረገበትም።

ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተደረገበት እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከተጋጣሚያቸው የተሻለ ብልጫ የወሰዱበት ነበር።

በአጋማሹ የተጫዋች ለውጥ ካደረጉ በኋላ ከኳስ ቁጥጥር ብልጫ ባሻገር ዕድሎችን መፍጠር የጀመሩት ፈረሰኞቹ ተገኑ ተሾመ አመቻችቶት ከግቡ ቅርብ ርቀት የነበረው ሀብታሙ ጉልላት ካደረገው ሙከራ እንዲሁም መሳፍንት ጳውሎስ ከመዓዝን ምት ያሻማውን ኳስ ተጠቅሞ ፍፁም ጥላሁን በግምባር ከሞከረው አጋጣሚ በኋላ መሪ የሆኑበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል፤ መሳፍንት ጳውሎስ ከመዓዝን አሻምቷት ፍፁም ጥላሁን በግምባር ያስቆጠራት ግብም ፈረሰኞቹን ወደ መሪነት ያሸጋገረች ግብ ነች።

ከግቡ በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት በተሻለ መንገድ ማጥቃት ከሚጠበቅባቸው አዳማ ከተማዎች ይልቅ ፈረሰኞቹ የተሻለ ብልጫ የወሰዱበት ክፍለ ጊዜ ሲሆን ተቀይሮ ገብቶ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረገው ብሩክ አለማዮህ ያደረጋቸው ሙከራዎችም ተጠቃሽ ናቸው። ጥቂት የግብ ሙከራዎች የተደረገበት የሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታም በቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።