መቐለ 70 እንደርታ በኢትዮጵያ ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብ ባስተናገደበት ጨዋታ ላይ ቦዲቲ ከተማን 3 ለ 2 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ተሸጋገረ

9 ሰዓት ሲል በአዲስ አበባ ስታዲየም የተጀመረው
ይህ ጨዋታ ከጅምሩ በፈጣን እንቅስቃሴዎች ታጅቦ ነበር የጀመረው። መቐለ 70 እንደርታዎች በ14ኛው ደቂቃ በኬኔዲ ገብረፃዲቅ አማካኝነት ያደረጉት ሙከራ እንዲሁም ፕሪንስ ኦፈሬ ከመስመር አሻግሮት ቦና ዓሊ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስም የጨዋታው ቀዳሚ የግብ አጋጣሚዎች ነበሩ።
በ25ኛው ደቂቃ ላይም በጅማሮው ጥራት ያላቸውን ዕድሎች ለመፍጠር ሲቸገሩ የታዩት ቦዲቲ ከተማዎች ሳይጠበቁ መሪ መሆን ችለዋል። ከመዓዝን የተሻማውን ኳስ ትዕዛዙ መንግስቱ መቶት በግቡ አግዳሚ ቢመለስም መስመር ላይ ሲጠባብቅ የነበረው ሙሉቀን ተስፋዬ ኳሷን በቀላሉ ከመረብ ጋር በማገናኘት ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው። ግቧም በመቐለ 70 እንደርታ የኢትዮጵያ ዋንጫ ተሳትፎ ታሪክ ቡድኑ ላይ የተቆጠረች የመጀመሪያ ግብ ሆናለች።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ይበልጥ ተጭነው መጫወት የጀመሩት መቐለዎች በ37ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ አግኝተዋል። ፍፁም ዓለሙ ከመሃል ሜዳ በረጅሙ ተሻግራ ቦና ዓሊ በደረቱ አብርዶ ካመቻቻት በኋላ የቦዲቲ ተከላካዮች አታሎ በማለፍ ያስቆጠራት ግብም ምዓም አናብስትን አቻ ማድረግ ችላለች።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩት
ማስተዋል ጋቸፎ ተከላካይ አልፎ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ትዕዛዙ መንግስቱ ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሳይጠቀምባት የቀረው ወርቃማ አጋጣሚም ቦዲቲዎችን በድጋሚ ወደ መሪነት ለማሸጋገር የተቃረበች አጋጣሚ ስትሆን አጋማሹም 1ለ1 ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ፉክክር የተደረገበት እንዲሁም ምዓም አናብስቱ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ሲሆን ብልጫ ከወሰዱበት የአጋማሹ የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜ በኋላም 71 ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል።
ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ፍፁም ዓለሙ
በግሩም መንገድ ወደ ሳጥን ይዟት የገባውን ኳስ አባተ አለሙ ከጨረፋት በኋላ መቷት ግብ ጠባቂው ሲመልሳት ከግቡ አፋፍ የነበረው ፕሪንስ ኦፊሬ በቀላሉ ከመረቡ ጋር አዋህዶ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ምዓም አናብስት መሪነቱን ከተረከቡ በኋላም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና የፈጠሩ ሲሆን ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ቦና ዓሊ ተቀይሮ የገባው ሚሊዮን ወልዴ ከሳጥኑ ቀኝ ክፍል ያሻገራትን ኳስ ተጠቅሞ ባስቆጠራት ግብ መሪነታቸውን ወደ ሦስት ከፍ አድርገዋል።
ወደ ጨዋታ ለመመለስ በተሻለ መንገድ ማጥቃት የጀመሩት ቦዲቲዎች አጥናፉ ቡቼና 80ኛው ደቂቃ ላይ ካመከነው ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸው ወርቃማ አጋጣሚ በኋላ 90ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ በለጠ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ ባስቆጠረው ግብ ልዩነቱን ማጥበብ ችለዋል። አምስት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታም መቐለ 70 እንደርታ ቦዲቲ ከተማን 3ለ2 ሆነ ውጤተ አሸንፎ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግማሽ ፍፃሜ መሻገር ችሏል።

