በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ኩራት የሆነውና በታሪክ ድምቀቱ የሚታወቀው ታላቁ ደርቢ ዛሬ በአዲስ አበባ ስቴዲየም ለ51ኛ ጊዜ ሊከናወን ቀጠሮ ተይዞለታል።
ጨዋታውን ወደመዲናችን ለማምጣት ተራዝሞ በዛሬው ዕለት በተስተካካይ መርሃ ግብር የሚደረገው ይህ ተጠባቂ ፍልሚያ ገና በዋዜማው የስታዲየሙ ትኬቶች ሙሉ በሙሉ ተሸጠው መጠናቀቃቸው የስፖርት ቤተሰቡ ለጨዋታው ያለውን ከፍተኛ ናፍቆትና ጉጉት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በአሁኑ ሰዓት በደረጃ ሰንጠረዡ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ባሳዩት አቋም 3 ድሎችን፣ 1 አቻ እና 1 ሽንፈት አስመዝግበዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርጎ በቅርቡ እያሳየው ያለው የአሸናፊነት ስነ ልቦናው እንደ ጥሩ ጎን ቢታይም በተለይም በጨዋታዎች መገባደጃ ላይ የሚታይበት የተከላካይ ክፍል መዘናጋት እና ግቦችን በቀላሉ የማስተናገድ ክፍተት አሁንም እንደ ዋነኛ ድክመት ይነሳበታል።

ቡናማዎቹ በበኩላቸው ውድድሩ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ሽንፈት ያላስተናገዱበትን ድንቅ ጉዞ ይዘው ለዛሬው ደርቢ ቀርበዋል። ኢትዮጵያ ቡና በደረጃ ሰንጠረዡ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ያስመዘገባቸው 3 ድሎች፣ 1 አቻ እና 1 ሽንፈት ቡድኑ በቀላሉ የማይበገር መሆኑን ያሳያል። በአጭር ቅብብል ላይ የተመሰረተው የጨዋታ ፍሰታቸው እና በመሀል ሜዳ የሚፈጥሩት ብልጫ ለተጋጣሚ ፈታኝ ጥንካሬያቸው ቢሆንም የተገኙ በርካታ የግብ እድሎችን በአግባቡ ወደ ውጤት የመቀየር ድክመት ግን አሁንም የቡድኑ ትልቁ የቤት ስራ ሆኖ ቀጥሏል።
በአጠቃላይ በሁለቱ ተቀናቃኞች መካከል የሚደረገው ይህ የ51ኛው የደርቢ ጨዋታ በበርካታ ደጋፊዎች ህብረ ዜማ ታጅቦ 9:00 ሲል ጅማሮውን ያደርጋል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሊጉ 50 ጊዜ ተገናኝተዋል። በእነዚህ ግንኙነቶች ፈረሰኞቹ 22 ጊዜ ድል ሲቀናቸው ቡናማዎቹ 9 ጊዜ አሸንፈዋል፤ 19 ጊዜያት ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት በድምሩ 98 ጎሎች መረብ ላይ አርፈዋል። 64 ግቦችን በማስቆጠር ፈረሰኞቹ ቀዳሚ ሲሆኑ ቡናማዎቹ ደግሞ 34 ኳሶችን ከመረብ አዋህደዋል።

