ቡናማዎቹ ከመመራት ተነስተው ፈረሰኞቹን 3 ለ 1 በማሸነፍ በተጠባቂው የደርቢ ጨዋታ ባለ ድል ሆነዋል።
በበርካታ ደጋፊዎች ሕብረ ዝማሬ በደማቅ ድባብ ታጅቦ የተካሄደው የ20ኛው ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ቡድኖቹ በጥሩ መነቃቃት ቀዳሚ ለመሆን የተንቀሳቀሱበት ቢሆንም ሁለቱም በተመሳሳይ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ጨዋታው 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም ወደፊት በመሄድ ረግድ በአንፃራዊነት የተሻሉ የነበሩት ፈረሰኞቹ ቀዳሚ መሆን ችለዋል፣ ፍፁም ጥላሁን አማካዩ ሀብታሙ ጉልላት ሳጥን ውስጥ በቀላሉ በተከላካዮች መካከል ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም ቡድኑን መሪ ማድረግ ችላለች።

ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ አሰሳ ጫና የፈጠሩት ቡናማዎቹ ዲቫይን ዋችኩዋ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ባደረገው እንዲሁም አቡበከር አዳሙ በሞከረው ጠንካራ ሙከራ በኋላ ጭማሪ ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ኦካይ ጁል አምበሉ ራምኬል ጀምስ ካሻገራት በኋላ ያብስራ ጎሳዬ የጨረፋትን ኳስ አግኝቶ በግሩም ሁኔታ መሬት ለመሬት መቶ ያስቆጠራት ግብም ቡናማዎቹን አቻ ማድረግ የቻለች ግብ ነች። ብርቱ ፉክክር የተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽም በአቻ ውጤት ተገባዷል።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ቀጥሎ ጅማሮው ላይ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት ቡናማዎቹ 53ኛው ደቂቃ ላይ መሪነቱን መረከብ ችለዋል። ፉአድ ኢብራሂም ከራሱ ሜዳ ክልል ያሻገረውን ኳስ አቡበከር አዳሙ በግምባሩ ከጨረፈው በኋላ ቢኒያም ጌታቸው ሾልኮ በመውጣት መረብ ላይ ያሳረፋት ግብም ቡድኑም መሪ ማድረግ ችላለች።

ቡናማዎቹ መሪነቱን ከተረከቡ በኋላ ፈረሰኞቹ የተሻለ ጫና መፍጠር ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር የቻሉት ግን ኢትዮጵያ ቡናዎች ናቸው፤ ዘላለም አባተ 66ኛው ደቂቃ ላይ ከመዓዝን ተሻግራ ተከላካዮች የመለሷትን ኳስ ተጠቅሞ በ’ቮሊ’ ያስቆጠራት ኳስም የቡናማዎቹን መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የቻለች ግብ ነች።

ፈረሰኞቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ ሀብታሙ ጉልላት ከሳጥኑ ጠርዝ ሆኖ ባደረገውና ግብ ጠባቂው እንደ ምንም ጨርፎ ባወጣው ሙከራ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ በቡናማዎቹ 3ለ1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

