77ኛው የፊፋ ጠቅላላ ጉባኤ በአፍሪካ ምድር ሞሮኮ ላይ እንደሚከናወን ተገልጿል

የዓለም የእግርኳስ የበላይ አካል የሆነው ፊፋ ሰሞኑን ካናዳ ላይ 76ኛውን ጠቅላላ ጉባኤ እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። ከወዲሁ በጉጉት የሚጠበቀውና 77ኛው ኮንግረስ ደግሞ አፍሪካ ላይ እንዲከናወን መወሰኑ ተሰምቷል።
አህጉራዊ እና ዓለምአቀፋዊ መድረኮችን እያስተናገደች የምትገኘው ሞሮኮ ይህ ታላቅ ስፖርታዊ ሁነት ሀገሪቷ በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረክ እያሳየች ያለችውን ጠንካራ ተሰሚነትና ዝግጁነት የሚያሳይ እንደሆነ ተመላክቷል። በተለይ በቅርብ ዓመታት በስፖርት መሰረተ ልማትና በዲፕሎማሲው ዘርፍ እያከናወነች ያለችውን ውጤታማ ስራ የሚያንፀባርቅ እንደሆነ ተጠቁሟል።

የ2027ቱ የፊፋ ኮንግረስ ላይ ቀጣዩ የፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚካሄድ ሲሆን ሁነቱም በመላው የእግርኳስ ቤተሰብ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ስለሆነ ጉባኤው ከመላው ዓለም የተወጣጡ የእግር ኳስ አመራሮችንና ባለድርሻ አካላትን ወደ ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር የሚስብ በመሆኑ ሀገሪቷን የበጎ ትኩረት ማዕከል ያደርጋል።
ከፖርቹጋል እና ስፔን ጋር በመሆን የ2030 የዓለም ዋንጫ እንድታስተናግድ የተመረጠችው ሞሮኮ ይህ ዓለምአቀፋዊ መድረክ ትልቅ መነቃቃት እንደሚፈጥርላት ይገመታል።

