ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ29ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ29ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

29ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጠናቀቃል፤ ጨዋታዎቹ የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል

ቅዲስ ጊዮርጊስ ከ ሲዳማ ቡና

ባለፈው እሁድ በተካሄደው የ20ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐ ግብር ከአራት ሽንፈት አልባ ጨዋታዎች በኋላ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት የገጠማቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሦስት ደረጃዎች የሚያሻሽሉበትን ዕድል ለማመቻቸት ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ይፋለማሉ። በሰላሣ አምስት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ ሦስት ነጥብ ብቻ ከሰበሰቡባቸው ስምንት ድል አልባ ሳምንታት በኋለ ባደረጓቸው ጨዋታዎች በብዙ ረገድ ተሻሽለዋል። ቡድኑ ምንም እንኳን በመጨረሻው ተጠባቂ ጨዋታ ሽንፈት ቢያስተናግድም ስምንት ግቦች ባስቆጠረባቸው ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች ያሳየው እንቅስቃሴ እና መሻሻል ግን በአወንታነቱ ይጠቀሳል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረውን የሊጉ መሪ በሚገጥምበት የዛሬው ጨዋታም በመጨረሻው መርሐ ግብር የተስተዋሉትን የመከላከል ድክመቶችን ማረም ይኖርበታል።

በሁለተኛው ዙር ኮስታራ የዋንጫ ቡድን መሆኑን እያሳየ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ከተከታዩ መቻል ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ዳግም ወደ አስር ከፍ ለማድረግ ፈረሰኞቹን ይገጥማል። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ዘጠኝ ጨዋታዎች ስድስት ድል፣ ሁለት ሽንፈት እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ከዚህ ቀደም የነበረባቸው የወጥነት ችግር የቀረፉት ሲዳማ ቡናዎች ባስመዘገቧቸው ድሎች እንዲሁም ተከታዮቻቸው በሁለተኛው ዙር በገጠማቸውን የውጤት ማሽቆልቆል መሪነታቸው ማደላደል ችለዋል። በጥሩ ወቅታዊ አቋም የሚገኘው እና በመጨረሻው መርሐ ግብር ከደረሰበት ሽንፈት ለማገገም ወደ ጨዋታው የሚቀርበውን ቅዱስ ጊዮርጊስ በሚገጥሙበት የዛሬ ጨዋታም በቅርብ ሳምንታት ያሳዩትን ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት ማስቀጠል ይጠበቅባቸዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም፤ ሲዳማ ቡናዎች ግን አጥቂው አቤል ያለውን ከቅጣት ምክንያት አያሰልፉም ሀብታሙ ታደሰም ከረዥም ጊዜ ጉዳት በኋላ ወደ ልምምድ ተመልሷል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 31 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 18 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው በአንፃሩ ሲዳማ ቡና 3 ጊዜ አሸንፏል። 10 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተጠናቋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 40 ሲዳማ ቡና ደግሞ 14 ጎሎችን አስመዝግበዋል።

ባህርዳር ከተማ ከ ሽረ ምድረ ገነት

በ28ኛው ሳምንት መርሐ ግብር ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ በሸገር ከተማ ሽንፈት ያስተናገዱት ባህርዳር ከተማዎች ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ሽረ ምድረ ገነትን ይገጥማሉ። በሰላሣ ስድስት ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የጣና ሞገዶቹ በአምስት መርሐ ግብሮች በድምር ከተቆጠረባቸው የግብ መጠን በእኩሌታ ባስተናገዱበት የመጨረሻ ጨዋታ ላይ የመከላከል አደረጃጀታቸው በብዙ ረገድ ተዳክሞ ነበር። ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ከፍተኛ የግብ ማስቆጠር ችግር ያለበትን ቡድን እንደመግጠሙ በመከላከሉ ረገድ ከባድ ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ ባይገመትም በመጨረሻው መርሐ ግብር የተስተዋሉትን ግለሰባዊ እና መዋቅራዊ የመከላከል ድክመቶችን መቅረፍ ይኖርበታል።

በሀያ ዘጠኝ ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረ ምድረ ገነቶች ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ለመታረቅ ከጣና ሞገዶቹ ጋር ይፋለማሉ። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ካሸነፉበት የሀያ አንደኛው ሳምንት መርሐ ግብር በኋላ ባደረጓቸው ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባቸው ሀያ አንድ ነጥቦች ውስጥ ሦስቱን ብቻ ያሳኩት ሽረዎች በተለይም በማጥቃቱ ረገድ እጅግ ተዳክመዋል። በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረው ቡድኑ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በቀዳሚነት የማጥቃት አጨዋወቱን በማሻሻል የሚፈጥራቸውን የግብ ዕድሎች ቁጥር ከፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ባህርዳር ከተማ ማንያዘዋል ካሣ እና ወንድወሰን በለጠን በጉዳት ምክንያት ዛሬ አያገኝም። ሽረ ምድረገነቶች የስድስት ጨዋታዎች ቅጣት ከተላለፈበት ሽመክት ጉግሳ ውጭ በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

የተሰረዘው የ2012 ጨዋታ ሳይጨምር በሊጉ 5 ጊዜ የተገናኙት ቡድኖቹ ባህርዳር ከተማ 2 ጨዋታዎች ላይ ድል ሲያደርግ ምድረ ገነት ሽረ 1 ጨዋታ አሸንፎ በተቀሩት 2 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ባህር ዳር ከተማ 4 ግቦች ሲያስቆጥር ስሑል ሽረ 1 አስቆጥሯል።