“ብሔራዊ ቡድኑ እያደገ ነው።” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ

“ብሔራዊ ቡድኑ እያደገ ነው።” አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ

👉 “በአንድ ጊዜ ሁሉን ነገር አትሠራም…”

👉 “ብሔራዊ ቡድኑ እያደገ ነው…”

ከሁለተኛው የወዳጅነት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ የዋልያዎቹ አለቃ የሰጡትን አስተያየት እንዲህ አቅርበነዋል።

ከባለፈው የቀጠለው የማላዊ የወዳጅነት ጨዋታ ዛሬ በድሬዳዋ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ምሽት ላይ ተካሂዶ ጨዋታው በመጀመርያው አጋማሽ በተቆጠሩ ጎሎች አንድ አቻ መጠናቀቁ ይታወቃል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳሕሌ ለመገናኛ ብዙኀን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ያነሱትን ዋና ነጥብ እንዲህ አቅርበነዋል።

ከባለፈው ጨዋታ ዛሬ ቡድኑ ተሽሎ እንደቀረበ የገለጹት አሰሌጣኙ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ ለተስተዋለው የአጨራረስ ችግር “በአንድ ጊዜ ሁሉ ነገር አትሠራም። አሁን እኛ እያየን ያለነው ብሔራዊ ቡድኑ ላይ ዕድገት መሻሻል አለው። ባለፈው እነርሱ ሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን ተቆጣጥረውት ነበር። እኛ አፈግፍገን ነበር የምንጫወተው። ዛሬ ግን ሳናፈገፍግ ተጭነናቸው ብዙ ስህተት እንዲሳሳቱ አድርገናቸዋል። አጨራረስ ላይ ያለው ችግር ጊዜ ይጠይቃል”። ካሉ በኋላ “ቡድኑ በስነ ልቦናው ማደጉ እና በሁለቱ ጨዋታ ከእነርሱ በተሻለ ሁለት ጎል ማስቆጠራችን መሻሻላችን ያሳያል ብለዋል።”

ቡድኑ ላይ የቆሙ ኳሶች አጠቃቀም ላይ በተለይ (የቅጣት ምቶች) ጎሎችን ለማግኘት ውስንነት ይታያል እዚህ ላይ ምን ሊሠሩ ያስባሉ? እንዲሁም ወጣቶችን ልምድ ካላቸው ጋር በማጣመር ረገድ ምን ለመሥራት  ያስባሉ? ተብለው ሲጠየቁ በአጭሩ “ያልከውን እንቀበላለን” በማለት መልሰዋል።