ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ37ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች| የ37ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች

የሲቢኢ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 37ኛው ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይጀመራል። ላለመውረድ በሚደረገው ፉክክር ተጠባቂ የሆኑ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ መቐለ 70 እንደርታ

በ47 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቡናማዎቹ ደረጃቸውን ለማሻሻል ላለመውረድ እየታገሉ የሚገኙት ምዓም አናብስትን ይገጥማሉ። በመጨረሻው ሳምንት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያዩት ቡናማዎቹ ባለፉት ጨዋታዎች ወጥ የሆነ ውጤት ማስመዝገብ አልቻሉም፤ በዛሬው ጨዋታ ወደ ድል ለመመለስም አጥቂዎቹ የሚያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ወደ ግብነት በመቀየር ሊጉን በተሻለ ነጥብ ለማጠናቀቅ ያልማሉ።

በ37 ነጥብ 19ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው መቐለ 70 እንደርታ ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ ጨዋታ ከቡናማዎች ጋር ያደርጋል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች በተከታታይ ያለ ምንም ግብ አቻ በመለያየት ወሳኝ ነጥቦችን ጥሏል።  ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚያደርገው የዛሬው ጨዋታም በሊጉ የመትረፍ ያለውን ጠባብ ዕድል ለመጠቀም 3 ነጥብ ይዞ መውጣት ምንም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ቡድኑ ​ወደ ድል ጎዳና ለመመለስም ባለፉት ተከታታይ ጨዋታዎች የታየበትን ግልፅ የፊት መስመር ፍሬ አልባነት በአስቸኳይ መቅረፍ እና የግብ ማግባት ብቃቱን ማሻሻል ይኖርበታል። ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቡናን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር በጥንቃቄ መከላከል ከቡድኑ ይጠበቃል።

ከዚህ በፊት ቡድኖቹ በሊጉ ደረጃ ስምንት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ቡናማዎቹ በሁለት ጨዋታ ሲያሸንፉ ምዓም አናብስቶች በአንዱ ብቻ አሸንፈው ቀሪዎቹ አምስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በግንኙነታቸው 13 ግቦች የተቆጠሩ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና 8 ግብ መቐለ ደግሞ 5 ግቦችን መረብ ላይ አሳርፏል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

​ባለፈው የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ የደረሰበትን ሽንፈት ተከትሎ ከሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው አርባምንጭ ከተማ ዛሬ በሊጉ ለመቆየት የሞት ሽረት ትንቅንቅ ከሚያደርገው ወልዋሎ ይጫወታል። በፋሲል ከነማ ከደረሰባቸው ሽንፈት ለማገገም ወደ ሜዳ የሚቀርቡት አዛዎቹ በሊጉ ለመትረፍ ነጥብ ማስመዝገብ ከሚጠበቅበት ተጋጣሚያቸው በተሻለ ከማንኛውም ዓይነት ጫና ነፃ ሆነው ጨዋታቸውን ይከውናሉ።

በ42 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቢጫ ለባሾች በከርሞ በሊጉ ለመቆየት አስቀድሞ ከሊጉ መውረዱ ያረጋገጠውን አርባምንጭ ከተማን ይገጥማሉ።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና 1ለ0 የተሸነፉት እና በ17ኛ ደረጃ ከተቀመጠው ሽረ ምድረ ገነትን በሦስት ነጥብ ልቀው የተቀመጡት ቢጫዎቹ በሊጉ የመቆየት ተስፋቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መመለስ ግድ ይላቸዋል። ከሊጉ መውረዱን ካረጋገጠው አርባምንጭ ከተማ ጋር በሚያደርጉት የሞት ሽረት እና የህልውና ጨዋታም ባለፉት አራት ጨዋታዎች በአንድ አጋጣሚ ብቻ ኳስና መረብ ያገናኘውን የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማሻሻል ይኖርባቸዋል።

በሊጉ 5 ጊዜ የተገናኙ ሲሆን አዞዎቹ ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፉ ቢጫ ለባሾቹ አንድ አሸንፈዋል ቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎችን ደግሞ በአቻ ውጤት ተለያይተዋል። 12 ግቦች ሲቆጠሩ ሁለቱም ቡድኖች ስድስት ስድስት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።