ወልዋሎ ዓ/ዩ በአፍሪካ መድረክ በሚኖረው ውድድር እና የሰባ ዓመት ታሪካዊ በዓሉን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል

ወልዋሎ ዓ/ዩ በአፍሪካ መድረክ በሚኖረው ውድድር እና የሰባ ዓመት ታሪካዊ በዓሉን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል

👉 “የምንወክለው ሀገራችንን እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡና መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ እንጠይቃለን” አቶ አሮን ሀጎስ

👉 “ወልዋሎን የህዝብ ክለብ ለማድረግ እንቅስቃሴ ተጀምሯል” አቶ ሞገስ

👉 “በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ከዚህ ቀደም በሀገራችን ከነበረው ውጤት በተሻለ የምድብ ድልድል መግባት ዕቅዳችን ነው” አቶ ሞገስ

የኢትዮጵያ ዋንጫን ሐምሌ 2/2018 በማንሳት በሰባ ዓመት የምስረታ ታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ውድድር ሀገራችንን የሚወክሉት ወልዋሎዎች የዋና አሰልጣኛቸውን ግርማ ታደሰ ቅጥር፣ የሰባ ዓመት የምስረታ በዓላቸውን እና ወደፊቱ ክለቡን በፋይናንስ አቅም ለማጠናከር በታሰቡ ጉዳዮች ዙርያ ለማስፈፀም የተቋቋመው ዐብይ ኮሚቴ  ዛሬ ከሰዓት በካፒታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

በጋዜጣዊ መግለጫው መድረክ የክለቡ የቦርድ አባል አቶ አሮን ሀጎስ እና የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ እንዲሁም ሌሎችም የኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል። የመግቢያ ማብራሪያ ያደረጉት አቶ አሮን በንግግራቸው “ክለቡ የኢትዮጵያ ዋንጫን ማሳካቱን ተከትሎ የበዓል አከባበር ለማድረግ የተለያዩ ስራዎችን ለመስራት መታሰቡን እና ነገ የቡድኑ አባላት ወደ መቐለ እንደሚጓዙ እና የአቀበባል ስነ ሥርዓት እንደሚኖር በዓዲግራት በሚኖር ቆይታቸው የሽልማት እና ሌሎች ፕሮግራሞች መኖራቸውን” ገልፀዋል።

ከዚህ ባሻገር ዝግጅቱ በዚሁ እንደማያበቃ እና በቀጣይ “የሰባ ዓመት አከባበር ጋር በተያያዘ የመስቀል በዓል በትግራይ የሚከበር ትልቅ በዓል እንደመሆኑ ሰፊ ዝግጅት ለማድረግ ኮሚቴ ተዋቅሮ በአዲስ አበባ፣ በመቐለ እና በዓዲግራት ኮንሰርትና ሌሎች ዝግጅቶች እንደሚኖሩ እንዲሁም ክለቡ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ብዙ ዋጋ የከፈሉ ግለሰቦችን የዕውቅና የሽልማት ፕሮግራሞች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል።”

ክለቡን ሕዝባዊ ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት አቶ አሮን “የወልዋሎ ሕዝብ እግርኳስ ወዳድ እንደሆነ ይታወቃል ይህን ደግሞ ተጠቅመን የህዝብ ክለብ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን እና ክለቡ ራሱን በራሱ ባለቤትነት ህዝብ እንዲያስተዳድረው ለማድረግ ከነጋዴው ማህበረሰብ ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በማስተሳሰር ክለቡን ከተወሰኑ የመንግስት በጀቶች እንዲላቀቅ ለማደረግ በትኩረት እንደሚሰሩ አፅኖት ሰጥተው ገልፀዋል።

ክለቡ በቀጣይ በአፍሪካ መድረክ ለሚኖረው ተሳትፎ በፋይናንስ አቅሙ የጠነከረ እንዲሆን እና በቡድን ግንባታ ዙርያ የተለያዩ ቅድመ ዝግጅት ስራዎች እንደሚሰሩ አቶ ሞገስ አንስተው በዋናነት “ብዙ ስራ ይጠብቀናል ይህንንም በተጠና መልኩ ገቢ ለማሰባሰብ የኢትዮጵያ ዋንጫ ድሉን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ቡድኑን ለማጠናከር ስራዎች ጀምረናል ለዚህም ማሳያ አሰልጣኝ ግርማ ታደሰን ማቆየት ችለናል። በቀጣይ ደግሞ ከቡድኑ ጋር ዘንድሮ ያሳለፉትን ተጫዋቾችን ለማቆየት የቴክኒክ ኮሚቴው ከአሰልጣኙ ጋር በመሆን እንቅስቃሴ መጀመሩን ካነሱ በኋላ እንደሚታወቀው የምንወክለው ሀገራችንን እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡና መንግስት ድጋፍ እንዲያደርግ እንጠይቃለን” ብለዋል።

ከመገናኛ ብዙኀን የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን ምላሽ ተሰጥቶባቸው ጋዜጣዊ መግለጫው ተጠናቋል።