የኢትዮ ኤሌክትሪክ ቦርድ ጥሩ የውድድር ዓመት ያሳለፉትን አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታን በክለቡ እንዲቀጥሉ ወስኗል

ያለፉት ሁለት ዓመታት ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተረክበው በዋና አሰልጣኝነት የመሩት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በተለይ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ከብዙዎች ግምት ውጭ ሃምሳ አራት ነጥብ በመሰብሰብ አምስተኛ ደረጃ ይዘው በማጠናቀቅ ቡድኑ ከዓመታት በኋላ የተሻለ ውጤት አስመዝግቦ እንዲያጠናቅቅ አስችለውታል።
ይህን ከግምት ያስገባው የክለቡ ቦርድ ዛሬ ባደረገው ስብሰባ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ከቡድኑ ጋር እንዲቆዮ መወሰኑን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። አሰልጣኝ ዘሪሁን ከዚህ ቀደም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በዋና እና በምክትል አሰልጣኝነት ባገለገሉበት ዘመን በዋንጫ የታጀበ ስኬታማ ዓመታቶችን ያሳለፉ ሲሆን የሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ የመሆን ክብር ማግኘታቸው ይታወሳል።
ውላቸውን ለማራዘም የተስማሙት አሰልጣኙ ቡድናቸውን ለማጠናከር በቀጣይ ቀናቶች ወደ ዝውውሩ የሚገቡ ይሆናል።

