የግል አስተያየት | የዘገየ ውሳኔ እና የባከነ ዕድል | ክፍል አንድ

የግል አስተያየት | የዘገየ ውሳኔ እና የባከነ ዕድል | ክፍል አንድ

የኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ልማት ስትራቴጂ ፤ የዘገየ ውሳኔ እና የባከነ ዕድል …

በኢዝ-አሻራ

ሰሞኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከ2018 እስከ 2020 ዓ.ም የትግበራ ቆይታ የሚኖረው የሴቶች እግር ኳስን በታዳጊዎች ደረጃ መሠረት ከመጣል ጀምሮ እስከ ብሔራዊ ቡድን ያለውን እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ያለመ የሴቶች እግርኳስ ልማት ስትራቴጂ ይፋ አድርጓል፡፡ በእቅዱ ዝርዝር ይዘት ላይ ሊነሱ የሚገባቸው በርካታ በጎ ጥያቄዎችና ትችቶች  እንደሚኖሩ አምናለሁ፡፡ሆኖም የዚህ ፅሁፍ ዋና ዓላማና ትኩረት ፌደሬሽኑ ባዘጋጀው ዝርዝር የእቅድ ይዘት ላይ ጥያቄዎችንና ትንተናን ማቅረብ ሳይሆን የስትራቴጂውን ዓላማዎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ካዘጋጀው ስትራቴጂክ እቅዱ የዝግጅት ሂደቱና ወቅታዊነት እንዲህም ወቅቱን ባለመጠበቁ ያመለጡ እድሎችን ማሳየት፣ በመዘግየቱ ከእቅዱ ጀርባ ያሉ ውስጣዊና ውጫዊ ሀቆች፣ እቅዱ ያለውን ተስፋና ስጋቶች ማሳየት በተጨማሪም በንፅፅር የጎረቤት ሀገራት ተጠቃሚነትን በጥቂቱ ማሳየት ላይ ያተኮረ ነው፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ቤተሰቡ እንዲረዳው አተገባበሩ እጅግ ሰፊና ጥልቅ የልማት ፖሊሲዎችና ፅንሰ ሀሳቦችን የያዘውን የፊፋን የ10 ዓመት የሴቶች እግር ኳስ ልማት ስትራቴጂዎችን በመነሻነት ሳይቃኝ ወደ ሀገራችን ስትራቴጂ እቅድ መግባት የዚህን ፅሁፍ ዕይታ ከማሳነሱ በላይ በዚህ ፅሁፍ የሚነሱ ሀሳቦችን ሚዛን መስጠበቅ አይችሉምና ለኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ቤተሰብ የተሻለ ግንዛቤ ምስል እንዲፈጥር በዚህ ክፍል –

* የፊፋ የሴቶች እግርኳስ ስትራቴጂ ዓላማዎች ምንድናቸው ?

* 5ቱ የስትራቴጂው ማስፈፀሚያ ምሶሶዎች ምን ምን ጉዳዮችን ያካትታሉ?

* የፊፋ የሴቶች እግር ኳስ ልማት ፕሮግራሙን ለማስፋት የተጨመሩት 5ቱ ኢንሼቲቮችስ ምን ምን ናቸው?

* ስትራቴጂውን ለማስፈፀም ከአባል ሀገራት ምን ይጠበቃል?

የሚሉትን አስቃኛለሁ መልካም ንባብ

የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (FIFA) የሴቶች እግር ኳስን ወደ አዲስ የዕድገት ደረጃ ለማሸጋገር ፊፋ የሴቶች እግር ኳስ ስትራቴጂን እ.ኤ.አ. በጥቅምት 9 ቀን 2018 አስጀምሯል። 211 ዱም አባል ሀገራትን ተጠቃሚ የሚያደርገው ይህ የ10 ዓመት ስትራቴጂ እቅድ ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች ማለትም ተሳትፎን ማሳደግ /Grow Participation/ በዓለም ዙሪያ የሴት ተጫዋቾችን ቁጥር ለመጨመር።  የንግድ ዋጋን ማሳደግ /Enhance the Commercial Value/ አዳዲስ የገቢ ምንጮችን ፈጥሮ፣ የሴቶችን ውድድር ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ማሳደግ እና መሠረት መገንባት / Build the Foundations/ ለሴቶች እግርኳስ ጠንካራ ሥርዓት ፈጥሮ፣ ሴቶችን ወደ አመራር ሚና ማምጣት የሚሉ ዓላማዎችን ያቀፈ እና እነዚህን ዓላማዎች ለማስፈፀም የሚከተሉትን አምስት ምሰሶዎች ማለትም

1. ማልማትና ማሳደግ (Develop & Grow)

ፊፋ ሴቶች እግር ኳስ ወደ ማይጫወቱበት አካባቢዎች ጭምር ለማስፋፋት እና የሚጫወቱበትን ቦታ ለማሻሻል ሰፊ ፕሮግራሞች ዘርግቷል። “ፊፋ ፉትቦል ፎር ስኩልስ” (F4S) ፕሮግራምን ጨምሮ ከ90 በላይ የሀገር ማኅበራት ተጠቃሚ ሆነዋል፤ ወደ 1.5 ሚሊዮን ኳሶች ለልጆች ማሰራጨቱን የሰትራቴጂውን 5ኛ ዓመት ባበሰረበት ሪፖርቱ ላይ አሳውቋል። በዚህ ምሰሶ ፊፋ ለ211 አባል ሀገራት የባለሙያዎች እና መሣሪያዎች ድጋፍን ጨምሮ ፈንድና ቴክኒካዊ ድጋፍ ማድረጉን ሪፖርት አድርጓል።

2. ጨዋታውን ማሳየት (Showcase the Game)

ዓላማው የሴቶች እግርኳስ ተጫዋቾች፣ ለደጋፊዎችና ለንግዱ አካላት ራሳቸውን የሚያሳዩበትን የተለያዩ መድረኮች መፍጠር ሲሆን። ፊፋ አዳዲስ ውድድሮችን (ለምሳሌ ፊፋ ዊሜን’ስ ፉትሳል ወርልድ ካፕ) ፈጥሯል። በዚህ ዘርፍ የሴቶች ብሔራዊ ቡድኖች ቁጥርንም ከ2019ዓ.ም. ሲነጻጸር ከ155 ወደ 188 ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልፃል።


3. ማስተዋወቅና ንግድን ማሳደግ Communicate &
Commercialese)

ፊፋ ታኅሣሥ 2021 የሴቶች እግርኳስ ለብቻው ያቀፈ የመጀመሪያ የንግድ ሽርክና ፕሮግራም ጀምሯል። የ2023ቱ ዓለም ዋንጫ ለዚህ ተግባሩ ዋንኛ ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ በዚህ ማሰተዋወቅና ንግድን ማሳደግ ምሶሶ 30 የስፖንሰር ሽርክናዎችን ማሳተፍ በመቻሉ እ.ኤ.አ. ከ2019 ጋር ሲነጻጸር ከ100% በላይ ዕድገትና ጭማሪ ማሳየቱን ፊፋ በሪፖርቱ አመላክቷል።

4. ማስተዳደርና ​መምራት (Govern & Lead)

በዚህ ምሰሶ ፊፋ ሴቶችን ወደ ከፍተኛ ወሳኝ የውሳኔ ሰጪነት ለማምጣት የቆረጠበት ነው። በዚህም “FIFA Women in Football Leadership Programme” ሴቶች አስተዳዳሪዎችን፣ ባለሙያዎችን በብቃት ለማብቃት እና ሙያዊ ትስስርን ለማሳደግ እንዲያገለግል እየሰራበት የሚገኝ ነው።

5. ማስተማርና ማብቃት (Educate & Empower)

ይህ ምሰሶ ፊፋ (FIFA) በዓለም ዙሪያ ባሉ ሴቶች እና ልጃገረዶች ህይወት ውስጥ በጎ ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት ያለውን አቻ የሌለው አቅም ለማጉላት የሴቶች እግር ኳስን እና ውድድሮችን ኃይል የተጠቀመበት ነው። ስትራቴጂው ሴቶችን ሜዳ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ቢሮ ውስጥ፣ ትምህርት ቤት ውስጥ፣ እና ማኅበረሰቡ ውስጥ ለማብቃት ያለመ ሁለ ገብ ዕቅድ ነው።

ባደሰበት ወቅት “ፉትቦል ዩናይትስ ዘ ወርልድ ፤ ስትራቴጂክ ኢኒሼቲቭስ ፎር ዘ ግሎባል ጌም” በሚል ቀደም ሲል በነበሩት ላይ 5 ተጨማሪ ኢኒሴቲቮችን አካትቷል።

እነሱም

1ኛ የሴቶች ጤና እና ደህንነት (Female Health & Wellbeing) ለሴት ተጫዋቾች አካላዊ እና ባዮሎጂያዊ ፍላጎት የተዘጋጀ የህክምና፣ የስነ-ምግብ፣ የጉዳት መከላከያ በተለይ የ-ACL/ጅማት ጉዳቶችን ለመቀነስ እና የወር አበባ/የወሊድ እንክብካቤን ያካተተ ሳይንሳዊ የጤና ድጋፍ ለመስጠት ያለመ።

2ኛ የፉትሳል እና የባህር ዳርቻ እግርኳስ ልማት (Futsal & Beach Soccer Development) ከመደበኛው 11 በ 11 እግር ኳስ ውጪ በቤት ውስጥ (Futsal) እና በባህር ዳርቻ (Beach Soccer) የሴቶች ውድድሮችን፣ ሊጎችን እና ብሔራዊ ቡድኖችን ማቋቋም እና ማሳደግ።

3ኛ ተሰጥኦን ማውጣት እና ማልማት (Talent Identification & Development) ልዩ ክህሎት ያላቸውን ታዳጊ ሴት ተጫዋቾች ገና በለጋ እድሜያቸው ለይቶ በማውጣት እና ስልታዊ የልማት መስመር (Talent Pathway) በመዘርጋት ወደ ከፍተኛ ፕሮፌሽናል ደረጃ የሚሸጋገሩበትን እድል ማመቻቸት።

4ኛ ደህንነት እና ጥበቃ (Safeguarding & Player Protection) ስፖርቱ ለሴት ተጫዋቾች፣ አሰልጣኞች እና ዳኞች ከማናቸውም አይነት ስነ-ልቦናዊ፣ አካላዊ ወይም ፆታዊ ጥቃቶች እና ትንኮሳዎች ነፃ የሆነ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ እንዲሆን የማስገደጃ ፖሊሲዎችን መተግበር።

5ኛ የንግድ እና ማርኬቲንግ አቅም ግንባታ (Commercial & Marketing Capacity) ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የሴቶች እግር ኳስን በራሱ የንግድ ማዕቀፍ እንዲያስተዋውቁ፣ አዳዲስ ስፖንሰሮችን እንዲስቡ እና ራሱን የቻለ የገቢ ምንጭ እንዲፈጥሩ የሚያስችል የቴክኒክ እና የማርኬቲንግ ድጋፍ ማድረግን ያለመ ነበር።

አባል ሀገራት የስትራቴጂውን ድጋፍ ለማግኘት
ምን ምን ዋና ዋና ደረጃዎችን ማለፍ ይኖርባቸዋል?

እንግዲህ አንድ ብሔራዊ ፌዴሬሽን ለምሳሌ፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከላይ የተቀመጡትን ኢኒሼቲቮች  ድጋፉን ለመጠየቅ ወይም ለማግኘት በመጀመሪያ ደረጃ ቅድመ ሁኔታ እና መዋቅራዊ መሰረቱን ታሳቢ በማድረግ የሴቶች እግር ኳስ ስትራቴጂ ማዘጋጀት ይኖርበታል ፌዴሬሽኑ የራሱን የ3 ወይም የ4 ዓመት የሴቶች እግር ኳስ መሪ እቅድ ማዘጋጀት እና በሥራ አስፈፃሚ በኩል ማጽደቅ አለበት። በተጨማሪም ራሱን የቻለ የሴቶች እግር ኳስ ክፍል ማቋቋም እና በሙሉ ጊዜ የሚሰራ ኃላፊ መመደብ ይኖርበታል ሲል የፊፋ የፕሮግራሞቹ ፍንድ አጠቃቀም ያሳያል።

በሁለተኛ ደረጃ የፍላጎት ዳሰሳ እና የፕሮግራም ምርጫ ማድረግ የሚኖርበት ሲሆን አንድ አባል አገር ከፊፋ 8 የሴቶች ልማት ፕሮግራሞች ውስጥ ለምሳሌ፡ የሊግ ማሻሻያ፣ የአሰልጣኞች ስልጠና፣ የሴቶች ጤና፣ ወዘተ በማለት የሀገሪቱን ቅድሚያ ፍላጎት መለየት አለበት። ፍላጎቱን ከለየ በኋላ ግልጽ የበጀት ዝርዝር፣ የተግባር ጊዜ ሰሌዳ እና የሚጠበቁ ውጤቶችን የያዘ የፕሮጀክት ሰነድ ማዘጋጀትም አለበት።

በሦስተኛ ደረጃ በፊፋ ፖርታል (FIFA MA Portal) ማመልከት

በ4ኛ ደረጃ የፊፋ የቴክኒክ ግምገማ እና ማጽደቅ ከዛም በኛና 6ኛ ደረጃ ድጋፉን መቀበል እና መተግበር እንዲሁም የኦዲት እና የሂደት ሪፖርት የማቅረብ ደረጃዎችን ማለፍ ይጠበቅበታል በተለይ ይህ ሪፖርት ለቀጣዩ ምዕራፍ ገንዘብ መለቀቅ እና ለተጨማሪ ፕሮግራሞች ማመልከቻ መፈቀድ ዋና መስፈርት ሆኖ ያገለግላል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዕቅድ ወቅቱን ባለመጠበቁ ከአለም አቀፉ ስትራቴጂ እቅድ ቀሪ ግዜ አንፃር ይሳካ ይሆን? ምን ተስፋ አለው? ፈተናዎቹስ? ባይሳካ ምን ዋጋ ያስከፍለናል? ሌሎች ሀገራት በተለይ ጎረቤት የምስራቅና የመካከለኛ አፍሪካ አገራት በዚህ ስትራቴጂ ምን ተጠቀሙ እንዴት? የሚሉትን ጉዳዮች ደግሞ በሚቀጥለው ክፍል ይዤ እመጣለሁ መልካም ጊዜ፡፡