በካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክለው ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዙር የማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹን የት እና መቼ እንደሚያደርግ ታውቋል።

የ2018 የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ የሆነውና በካፍ የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ሀገራችንን የሚወክለው ወልዋሎ ዓ/ዩ 70ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን እያከበረ በውድድሩ እንዲሁም በሀገር ውስጥ ውድድሮች የተሻለ ሆኖ ለመቅረብ ስብስቡን አጠናክሮ ዝግጅቱን ሊጀምር ሲሆን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚያደረገው ውድድር ላይም የመጀመሪያውን ዙር የማጣሪያ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚያደርግበት ሜዳ እና ጊዜን ሶከር ኢትዮጵያ አጣርታለች።
በዚህም ወልዋሎ ከሱዳኑ ሂላል አል ሳህል ጋር የሚያደርገው የመጀመርያ ጨዋታ ዓርብ ነሐሴ 29 ኪጋሊ ፔሌ ስታዲየም ላይ ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ቅዳሜ መስከረም 2 በድሬዳዋ ስታዲየም እንደሚያከናውን ከክለቡ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

