የውጪ ሀገር ተጫዋች እንዳያስፈርሙ እግድ የተጣለባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች ቤልጂየማዊ አሠልጣኝ ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

በ2019 የውድድር ዓመት በአዲስ መልክ ለመቅረብ ስብስቡን እያጠናከረ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ የቀድሞ አለቃውን ሰርዲዮቪን ሚሉቲን ሚቾ ዳግም በመንበሩ ካስቀመጠ በኋላ የተለያዩ አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሞ በአሠልጣኙ ተመራጭ የሆኑ ነባር ተጫዋቾችንም ውል አድሶ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ጀምረዋል። ባሳለፍነው ሳምንት አሠልጣኝ ሚቾ በይፋ ረዳቶቻቸውን ያስተዋወቂ ሲሆን በቡድናቸው ውስጥም ሁለት ከውጪ ሀገር የሚመጡ ረዳቶች እንዳሉ ጠቁመው ነበር። በጊዜው የሁለቱ ስም በዝርዝር ባይገለፅም ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት ቡድኑን የሚቀላቀለው የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ማን እንደሆነ መረጃ አግኝታለች።
የሰርዲዮቪን ሚሉቲን ሚቾ የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ በመሆን ፈረሰኞቹን የሚቀላቀለው ቤልጂየማዊው አሠልጣኝ ሞጆቪክ ራዴ ነው። በሰርቢያ የተወለደው እና ቤልጂየማዊ ዜግነት ያለው ሞጆቪክ ራዴ በተጫዋችነት በቤልጂየም አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን ለሚገኙ በርካታ ክለቦች እንዲሁም በስሎቬኒያ እና ዩጎዝላቪያ የአንደኛ ዲቪዚዮን ሊጎች የተጫወተ ሲሆን ከአስራ ስድስት አመታት በፊት ደግሞ ወደ አሠልጣኝነቱ ጎራ በማለት በሀገሩ ቤልጂየም አንደኛ እና ሁለተኛ ዲቪዚዮን እንዲሁም በሳውዲ አረቢያ ክለቦች ቆይታን አድርጓል። ከክለቦች በተጨማሪም በሊባኖን ብሔራዊ ቡድን በግብ ጠባቂ አሠልጣኝነት አገልግሏል።
የ55 ዓመቱ ራዴ ይህንን ዘገባ ባጠናከርንበት ሰዓት የፈረሰኞቹን ስብስብ ደብረዘይት ላይ የተቀላቀለ ሲሆን ከቀድሞ የክለቡ የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ዳንኤል የበላይ ሆኖ ቡድኑን እንደሚያገለግል ይጠበቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከፈረንሳይ ፔዤ እንደሚመጣ የተነገረው የፊትነስ እና የፐርፎንማንስ አማካሪ አሁን ክለቡን እንደማይቀላቀልና ከሳምንታት በኋላ መጥቶ ቡድኑን እንደሚያሰለጥን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

