“ጋዜጠኝነት ሰርቻለሁ ፤ ተምሬያለሁ። ባልሰራ እንኳን አውቀዋለሁ።”
አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከጋዜጠኞች ጋር በተገናኘ ተጨማሪ ሀሳብ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በጁፒተር ሆቴል እየሰጡ ያለውን መግለጫ ያጠናቀቁ ሲሆን ከጋዜጠኞች ጋር ስላላቸው ግንኙነት ቀደም ብሎ ካነሱት ሀሳብ በተጨማሪ ሌላ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። አሠልጣኙ በበርካታ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ስለጋዜጠኝነት እንደሚያውቁ ሲናገሩ እንደሚሰማ ተጠቅሶ ከጋዜጠኞች ጋር በተያያዘ ስላላቸው ልዩነት፣ ሰርቻለሁ ስላሉት የጋዜጠኝነት ሙያ ጥያቄ ቀርቦ ተከታዩን ብለዋል።
አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ “ከጋዜጠኞች ጋር በመርህ እንገናኝ ነው ያልኩት” ካሉ በኋላ “ሙያውን አውቀዋለሁ። ሙያውን አከብራለሁ። ኢቲካል በሆነ መንገድ ለሚመጣ ነገር ሁሉ መልስ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ፤ እኔን የሚመለከተኝ ጉዳይ ብቻ ላይ ነው መልስ የምሰጠው” በማለት ተናግረዋል።
አሠልጣኙ ከዚህ በፊት በጋዜጠኝነት ሰርቼ አውቃለሁ ማለታቸውን ተከትሎ የት እንደሰሩ ተጠይቀው አሠልጣኙ “አፍሮ ኤፍ ኤም በእንግሊዝኛ ሰርቻለው። አንዳንድ ጋዜጦች ላይም ፅሁፍ ፅፌያለሁ።” በማለት ተናግረዋል።
ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራት በጋዜጠኛ ቤተማርያም ኃይሉ በሚዘጋጀው ፉትቦል ፍሬንዚ ፕሮግራም አሠልጣኙ ተንታኝ ብቻ የነበሩ መሆኑን አውቀናል።

