👉 “በዕድል ሳይሆን በስራ ነው የማምነው”
👉 “…ስለዚህ እኛ ያንን 90 ደቂቃ ለመጫወትና ሦስት ነጥብ ወደ ቤታችን ይዘን ለመሄድ ተዘጋጅተናል”
👉 “እነሱ ደጋፊ እንዳላቸው ሁሉ እኛም ደጋፊ አለን ፤ ግን 90 ደቂቃው ነው ጨዋታውን የሚወስነው”

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዩሐንስ ሳህሌ ከወሳኙ ጨዋታ በፊት ጁባ ለሚገኙ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የቅድመ ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል። የቡድኑ አምበል የሰጠውን አስተያየት ቀደም ብለን ያቀረብን ሲሆን አሁን ደግሞ አሠልጣኙ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ እንደሚከተለው ይዘን መጥተናል።
ደቡብ ሱዳን ለሱዳን ጥሩ ዕድል አላት ፤ እዚህ መጥተን እናሸንፋለን። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አይነት አስተያየት አላችሁ?
“በዕድል ሳይሆን በስራ ነው የማምነው። በእግር ኳስ ሁሉም ጨዋታዎች የየራሳቸው ታሪክ አላቸው። ባለፈው ጊዜ የተፈጠረ ነገር ካለ ያ ያለፈ ነው። አሁን እኛ ለነገው ጨዋታ ተዘጋጅተናል። ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ዝግጁ ነን።”
በደቡብ ሱዳን ያለው የአየር ንብረት እንዴት አገኛችሁት?
“የአየር ንብረቱን መልመድ የግድ ይላል። እንደ ፕሮፌሽናል የአየር ንብረቱን መቆጣጠር ይገባናል።”
ከቡድኑ ጋር የተገናኘ የጉዳት ዜና አለ?
“23 ተጫዋቾች በቡድኑ ስብስብ ውስጥ አሉ። ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ሁሉም ጨዋታውን ለማድረግም ዝግጁ ናቸው።”
ተጋጣሚያችሁ የሱዳን ብሔራዊ ቡድንን እስከምን ድረስ ታውቁታላችሁ?
“ለተጋጣሚያችን የሱዳን ብሔራዊ ቡድንም ሆነ ለአሠልጣኙ ትልቅ ክብር አለኝ። በደንብ የተደራጀ ቡድን እንደሆነ እናውቃለን። የሽግግር ጨዋታዎችን እንደሚያዘወትሩ እናውቃለን። ግን እኛ ልምምዳችንን እና የቤት ስራችንን ሰርተናል። ስለዚህ የራሳችንን የጨዋታ መንገድ ለመተግበር ዝግጁ ነን።”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በምን አይነት መንገድ ጨዋታውን ሊቀርብ ይችላል?
“ቡድኑ በምንም አይነት መንገድ ቢደራጅ ዋናው ነገር 90 ደቂቃ ተጫውተህ ውጤት ይዘህ መውጣትህ ነው። ስለዚህ እኛ ያንን 90 ደቂቃ ለመጫወትና ሦስት ነጥብ ወደ ቤታችን ይዘን ለመሄድ ተዘጋጅተናል። ከአጨዋወት መንገድ ጋር ያለውን ነገር እዚህ ሳይሆን ሜዳ ላይ የምታዩት ይሆናል።”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ያላቸው ልምድ ምን ይመስላል?
“ልምድ ያላቸውም ሆነ ልምድ የሌላቸው ተጫዋቾች በቡድናችን ውስጥ ይገኛሉ። 7 እና 8 ዓመት በብሔራዊ ቡድኑ የተጫወቱ ተጫወቀቾች አሉ ፤ 2 አመትም እንዲሁ ለቡድኑ አዲስ የሆኑ ተጫዋቾችም በስብስባችን ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህን አቀላቅለን ነው ቡድኑን የሰራነው። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ከሳኦቶሜ ጨዋታ ጀምሮ ያሉ ናቸው። ስለዚህ እነዚህ ተጫዋቾች ጥሩ ነገር ይሰራሉ ብለን እናምናለን።”
ብሔራዊ ቡድኑ ከሜዳው ውጪ መጫወቱ የሚፈጥርበት ተፅዕኖ ይኖራል?
“ያለፉትን አምስት አመታት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁሉንም ጨዋታዎች ከሜዳው ውጪ ነበር ሲያደርግ የነበረው። በሜዳችን ተጫውተን አናውቅም። ምክንያቱም ሜዳችን ጨዋታዎችን እንድናደርግ ፍቃድ አላገኘም ነበር። ስለዚህ ጨዋታዎችን ውጪ እየወጣን ነበር ስናደርግ የነበረው ፤ ይህንን ተጫዋቾቻችን ያውቁታል። ይህ ብቻ ሳይሆን እዚህ ደቡብ ሱዳን እንደ ሱዳኖች ባይሆንም ብዙ ደጋፊዎች አሉን። ይህ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው። የተለየ ሀገር ከመጫወት እዚህ የተወሰኑ ደጋፊዎቻችን ያሉበት ቦታ መጫወታችን ለእኛ ጥቅም አለው። ዞሮ ዞሮ እነሱም ደጋፊ እንዳላቸው ሁሉ እኛም ደጋፊ አለን ፤ ግን 90 ደቂቃው ነው ጨዋታውን የሚወስነው።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባለፉት ጨዋታዎች ውጤታማ አለመሆኑ በነገው ጨዋታ የሚፈጥረው ነገር ይኖራል?
“እግርኳስ ጨዋታ የሚወሰነው በጨዋታው ቀን ነው። በትናንት አይደለም የሚወሰነው። ትናንት የነበሩት ነገሮች ሁሉ ታሪክ ናቸው። በ90 ደቂቃ የሚፈጠረው ነገር ነው ጨዋታውን የሚወስነው። እኛ ለ90 ደቂቃው ተዘጋጅተናል።”

