ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ቡድናቸውን ማጠናከር ቀጥለዋል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ቡድናቸውን ማጠናከር ቀጥለዋል

አንጋፋው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአራት ተጫዋቾችን ውል ሲያድስ አንድ ተጫዋች አስፈርሟል።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ዋንጫን በማሸነፍ በሴቶች ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ተሳታፊ የነበሩት እና በውድድሩ ብዙም ሳይጓዙ ከምድባቸው ሳያልፉ የቀሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች አንድ ተጫዋች ሲያስፈርሙ የአራት ተጫዋቾችን ውል አድሰዋል።

ውሏን ያደሰችው የመጀመሪያዋ ተጫዋች በፈረንሳዩ ሜትዝ የሙከራ ዕድል አግኝታ የነበረችው ንግሥት በቀለ ስትሆን አጥቂዋ ያደረገችው ሙከራ ባለመሳካቱ በክለቧ ለመቆየት ተስማምታለች።

ሌላኛዋ ውሏን ያደሰችው ተጫዋች ረድዔት አስረሳኸኝ ስትሆን ባለፈው የውድድር ዓመት የሊጉ ሁለተኛ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ መሆኗ ይታወቃል። ሦስተኛዋ ውሏን ያደሰችው በዋንጫ የታጀበ የእግርኳስ ሕይወት ያላት አንጋፋዋ አማካይ ሰናይት ቦጋለ ናት። አራተኛዋ ውሏን ያደሰች ተጫዋች ደግሞ የመስመር ተጫዋቿ ብዙዓየሁ ታደሠ እንደሆነች ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ቡድኑን የተቀላቀለችው አዲሷ ተጫዋች ደግሞ ያለፈውን የውድድር ዓመት በመቻል ያሳለፈችው ተከላካይዋ ሰናይት ሸጎ ስትሆን አምስቱም ተጫዋቾች በቀጣይ ሁለት ዓመታት በንግድ ባንክ ለመጫወት ነው ፊርማቸውን ያኖሩት።