👉 “ከኢትዮጵያ ጋር የምናደርገው የነገው ጨዋታ ትልቅ ጨዋታ ነው”
👉 “ጨዋታውን የምናደርገው በሁለተኛ ቤታችን ነው”
👉 “እዚህ ያሉት ተጫዋቾች የተሻለ ነገር ማድረግ ይችላሉ ፤ 100% የተሻለ ነገር ለመስጠት ዝግጁ ናቸው”
ነገ 10 ሰዓት በጁባ የሱዳን ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን በመግጠም የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ፍልሚያውን ይጀምራል። ከጨዋታው አንድ ቀን አስቀድሞም የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ክዌሲ አፒያህ የቅድመ ጨዋታ አስተያየታቸውን ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሰጥተዋል።
ጋናዊው አሠልጣኝ ክዌሲ አፒያህ “ከኢትዮጵያ ጋር የምናደርገው የነገው ጨዋታ ትልቅ ጨዋታ ነው።” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን አስከትለው በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ጨዋታ በተመለከተ ተከታዩን ብለዋል።
“ጨዋታውን የምናደርገው በሁለተኛ ቤታችን ነው። ደቡብ ሱዳናዊያን ቤተሰቦቻችን ናቸው። ሁሌ እዚህ ስንመጣ የደቡብ ሱዳናዊያንን ሙሉ ድጋፍ እናገኛለን። ሱዳናዊያንንም ደቡብ ሱዳናዊያንንም ደስተኛ ለማድረግ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ጨዋታው ቀላል ባይሆንም ድል ለማግኘት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ደቡብ ሱዳናዊያን እህት እና ወንድሞቻችን ናቸው። እዚህ ስንመጣ ቤታችን እንዳለን ነው የሚሰማን። በደንብ ነው የሚደግፉን።”

ከዝግጅት ጋር በተያያዘ አድካሚ ነገሮች በኖሩም በደንብ እንደተዘጋጁ የገለፁት የ66 ዓመቱ ታክቲሻን “ተጫዋቾቻችን ከተለያዩ አካባቢዎች ነው የመጡት። ትልቁ ነገር እንደ ቡድን ታክቲካሊ የተሻለ እንዲሆኑ ማድረግ ነው። ተጫዋቾቹ በአጭር ጊዜ ቢሆንም የተሰባሰቡት ለክለባቸውም ግልጋሎት መስጠት አለባቸው። በዚህ ሂደት ድካም ይኖራል። ድካም የዚህ ውድድር አካል ነው።” በማለት ከድካም ጋር እየታገሉ ቡድኑን ለነገው ፍልሚያ እንዳዘጋጁ ጠቁመዋል።
“ማንም ኖረ አልኖረ ዋናው ነገር እሱ አይደለም። እዚህ ያሉት ተጫዋቾች የተሻለ ነገር ማድረግ ይችላሉ። 100% የተሻለ ነገር ለመስጠት ዝግጁ ናቸው ፤ ይሄንንም እንደሚያደርጉ ሙሉ እምነት አለኝ።” በማለት በቡድናቸው እምነት እንዳላቸው የጠቆሙት አሠልጣኙ በሀሳባቸው መጨረሻ ዛሬ የ20 ዓመት በታች የሴካፋ ሻምፒዮን ስለሆነው የሱዳን ከ20 ዓመት በታች ቡድን እና የሱዳን የታዳጊ ቡድኖች ምልከታቸውን አጋርተዋል።
“ከባድ ነው። እንደ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ የውስጥ ሊግ ውድድሮችን ማየት ያስፈልጋል። በሌሎች ሀገር የሚጫወቱንም መከታተል ያስፈልጋል። አንዳንድ ጊዜ ተጫዋቾችህን በደንብ ስላሰለጠንክ ብቻ ለውጥ አታመጣም። በስነ ልንቦናም ረገድ ስራዎች ያስፈልጋሉ። በተናጥል ተጫዋቾቹ የተሻለ ነገር ሲኖራቸው ያንን አቀናጅቶ እንደ ቡድን ጥሩ ነገር መስራት ይቻላል። እንደ ሀገር ታዳጊዎች ላይ እየሰራን ነው። እኔም ረዳት አሠልጣኜን የ20 ዓመት በታች ቡድኑ ጋር ታንዛኒያ የላኩት በቅርበት እንዲከታተላቸው ነው። ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾች በቅርበት እየተከታተልን ቶሎ ወደ ዋናው ቡድን እያመጣን ልምድ እንዲያካብቱ እናደርጋለን።” በማለተ በወጣት ተጫዋቾች ትልቅ እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል።

