“ዋናው ነገር ዕድሉን ስታገኝ ዕድሉን የምትጠቀምበት መንገድ ነው” ክዌሲ አፒያ
ዋልያዎቹን አንድ ለምንም ያሸነፈው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ክዌሲ አፒያህ የሰጡትን የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ይዘን ቀርበናል።

በጁባ ብሔራዊ ስታዲየም የሱዳን ብሔራዊ ቡድን የኢትዮጵያ አቻውን ገጥሞ 1ለ0 በማሸነፍ የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጉዞውን በድል የጀመረ ሲሆን ከጨዋታው በኋላም የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ክዌሲ አፒያህ ከመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።
ስለጨዋታው
“ጨዋታው ትልቅ ጨዋታ ነው። በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረን ነበር ፤ ግን ግብ ማስቆጠር አልቻልንም። በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ በአንድ ሁለት አጋጣሚዎች መጥተው ነበር። እኛም ሁለት የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረን ነበር። እኛ ዕድለኛ ነበርን ፤ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ አስቆጥረን አሸንፈናል።”
የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ስለተደራጀበት መንገድ
“ችግሩ ይታወቃል። ሱዳን የራሷ የሆነ የሊግ ውድድር የላትም ፤ ግን በምንችለው መንገድ ብሔራዊ ቡድኑን በተሻለ ለማደራጀት እንሞክራለን። ደቡብ ሱዳን ቤታችን ነው። እዚህ እስከመጣን ጊዜ ድረስ ለደጋፊዎቻችን ጥሩ ነገር መስጠት አለብን። ደጋፊዎቻችንን ማስደሰት አለብን ብለን እናስባለን። በዛሬው ጨዋታ ላይ ተጫዋቾቻችን ድካም ይታይባቸው ነበር። በዚህ እነሱር መውቀስ አይገባም። ከዚህ የበለጠ ቡድኑ እያደገ ሲመጣ ደጋፊዎቻችንን ተበለጠ እያስደሰትን እንሄዳለን። ጨዋታዎችን ብዙ ባደረግን እና ጊዜ ባገኘን ቁጥር የበለጠ እየተዋሀድን እንሄዳለን።”
ደቡብ ሱዳንን ለጨዋታ ስለመረጡበት ምክንያት እና ስለቡድናቸው
“ደቡብ ሱዳንን የመረጥነው በርካታ ደጋፊዎች እዚህ ስላሉን ነው። በሜዳህ የምታደርገው ጨዋታ ላይ ደጋፊዎች ያስፈልጉሀል። ተጫዋቾቻችን የጨዋታ ዝግጁነታቸው ከዚህ የበለጠ መሆን አለበት። ለዚህ ደግሞ ጨዋታዎች ያስፈልጋሉ። ሱዳን የራሷን ሊግ እንደምትጀምር ተስፋ አደርጋለው። በዚህ ሂደት የተሻለ ቡድን ለመገንባት ይረዳናል። ትልቁ ችግር በሌላ ሀገር የሚገኙ ተጫዋቾችን ለሦሰት እና አራት ቀናት ብቻ ነው የምናገኘው። እርግጥ ይሄ ከሀገር ውጪ ብዙ ተጫዋቾች ላሏቸውም ብሔራዊ ቡድኖች ይሰራል። ግን እኛ ደግሞ በሀገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ስለሌሉን እነዛን የምናገኘው በትንሽ ቀን ስለሆነ ተፅዕኖ አለው።”
ጨዋታውን ስላሸነፉበት የፍፁም ቅጣት ምት
“በእግርኳስ ዕድል ዋጋ አለው። ብዙ እና የተሻለ ዕድል ስለፈጠርክ ብቻ አታሸንፍም። 10 እና 20 የግብ ዕድሎችን ስለፈጠርክ አይደለም ፤ ሦስት እና አራት የፍፁም ቅጣት ምትም አግኝተህ እነዛን ልትስት ትችላለህ። ዋናው ነገር ዕድሉን ስታገኝ ዕድሉን የምትጠቀምበት መንገድ ነው። ሜሲ እና ሌሎች ትልልቅ ተጫዋቾችም የፍፁም ቅጣት ምት ይስታሉ። አጠቃቀሙ ነው ወሳኙ ፤ ግን ደግሞ ዕድልም ዋጋ አለው።”

