👉 “ይሄንን ጥያቄ ለእናንተ (ጋዜጠኞች) እተወዋለሁ”
👉 “ጨዋታውን ቀድመን መጨረስ ነበረብን”
👉 “ከአጨራረስ ውጪ የነበረው የዛሬው እንቅስቃሴያችን ጥሩ ነበር”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሱዳን አቻው ጋር አድርጎ 1ለ0 በሆነ ውጤት ከተሸነፈ በኋላ የቡድኑ አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው
“ጨዋታውን መጀመሪያ ባገኘናቸው አጋጣሚዎች መጨረስ ነበረብን። ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ያገኘናቸውን ዕድሎች መጠቀም አልቻልንም ነበር። በሁለተኛው አጋማሽም ሁለት አጋጣሚዎች ነበሩን። እነሱንም መጠቀም አልቻልንም። በመጨረሻ ግን ሱዳኖች የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተዋል። ጨዋታውን ቀድመን መጨረስ ነበረብን።”
ስለፍፁም ቅጣት ምቱ
“አሁን ላይ ቪዲዮውን ካላየው ምንም ማለት አልችልም። ይሄንን ጥያቄ ለእናንተ (ጋዜጠኞች) እተወዋለው ፤ ቪዲዮውን አይታችሁ የራሳችሁን ሀሳብ እንድትሰጡ እተውላችኋለው። ነገርግን ሜዳ ከነበሩ ተጫዋቾቼ እና ጨዋታውን ካዩ ጋዜጠኞች እንደተረዳሁት ከሆን የፍፁም ቅጣት ምቱ እንደማያሰጥ ነግረውኛል። ምክንያቱም ተጫዋቹ ጥፋቱን አልሰራም። ነገር ግን የሆነው ሆኗል ፤ ሦስት ነጥቡን እነሱ ወስደዋል።”
ስታዲየሙ ውስጥ ስለነበረው ድባብ
“ስታዲየም ውስጥ የነበረው ድባብ እግርኳሳዊ ነበር። እነሱም ሱዳናዊ ደጋፊዎች ነበሯቸው ፤ እኛም የራሳችን ደጋፊዎች ነበሩን። በሁለቱም በኩል ትክክለኛ ደጋፊዎች ነበሩ። ምንም መጥፎ ነገር አልነበረም። ሁሉም የየራሱን ቡድን ሲደግፍ ነበር።”
ጨዋታው ስለተወሰነበት መንገድ
“የእግርኳስ አንድ አካል ነው። በፈጠርከው ዕድል ጨዋታውን ቀድመህ ካልጨረስክ ዋጋውን ትከፍላለህ። ዋጋውንም ከፍለናል። እነዛን የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ተጠቅመን ቢሆን ኖሮ ምናልባት ጨዋታውን እንቆጣጠረው ነበር። ይሄ ደግሞ ጨዋታውን ይቀይረው ነበር። በአጠቃላይ ይህ እግርኳስ ነው። ስህተት ከሰራህ ዋጋህን ትከፍላለህ።”
ስለቡድናቸው ክፍተት
“ከአጨራረስ ውጪ የነበረው የዛሬው እንቅስቃሴያችን ጥሩ ነበር። ዋናው ችግራችን አጨራረስ ነበር። ቀድመን በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጨዋታውን ብንጨርስ ኖሮ ጥሩ ነበር።”
ስለዳኝነት
“ስለዳኝነቱ ምንም ማለት አልፈልግም። ምክንያቱም እኛ ጨዋታውን መጫወት ነበረብን። ምናልባት ዳኛው የፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጥ ወይም ላይሰጥ እንዲሁም የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት ፍትሀዊ ነው አይደለም ልንል እንችላለን ግን የራሳችንን የቤት ስራ መስራትና ጨዋታውን ቶሎ መጨረስ ነበረብን። ጨዋታውን ቀድመን ብንጨርስ ኖሮ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ አንገባም ነበር።”
ሽንፈቱ ስለሚፈጥርባቸው ነገር
“ይሄ የ90 ደቂቃ ጨዋታ ነው።አሁን አልቋል። አንድ ጨዋታ ነበር አልቋል። አዎ ጨዋታውን ተሸንፈናል ፤ ግን አልቋል። ወደፊት አምስት ጨዋታዎች ይቀሩናል። እነዛን አምስት ጨዋታዎች ነው ማሰብ ያለብን። ብናሸንፍም ኖሮ ይሄ አልፏል በቃ። አሁን ከሦስት ቀናት በኋላ ከሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር ስላለን ጨዋታ ነው የምናስበው። ዳኛውም የፍፁም ቅጣት ምት ሰጥቶም ሆነ በሌላ መንገድ ጨዋታው አልቋል። አሁን ለቀጣዩ ጨዋታ ነው የምናስበው።”

