በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ፋሲል ከነማን 1ለ0 በማሸነፍ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ሲያስመዘግብ ዐፄዎቹ የውድድሩን መጀመሪያ ሽንፈት አስተናግደዋል።
በዐቢዩ አረጋሽ

በአብዮ ኤርሳሞ ስታዲየም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ በተካሄደው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም የግብ ሙከራዎቻቸው ወደ ውጤት ሳይቀየሩ አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዲያ ሆሳዕና የተሻለ ብልጫ በመውሰድ በተደጋጋሚ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት አድርጓል። ሆኖም የፋሲል ከነማን የመከላከል መስመር ሰብሮ መግባት ተስኖት ጨዋታው ወደ መጨረሻው ደቂቃ ተቃርቧል።
የጨዋታው ውጥረት ከፍ ብሎ በቀጠለበት ወቅት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ደስታ ዋሚሾ በተጨማሪ ደቂቃዎች 90+3 ላይ ከብርሃኑ አዳሙ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ለሀዲያ ሆሳዕና ወሳኝ ግብ አስቆጥሯል። ይህች ግብ ለቡድኑ የድል ደስታን ስታጎናጽፍ ለፋሲል ከተማ ደግሞ አሳዛኝ ሽንፈት ሆናለች።

በዚህም ሀዲያ ሆሳዕና በደስታ ዋሚሾ ብቸኛ ግብ 1ለ0 በማሸነፍ ወሳኝ ሶስት ነጥብ አግኝተዋል ፣ ፋሲል ከነማም የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት አስተናግዷል።

