ፈረሰኞቹ፣ ሐይቆቹ እና የጦና ንቦቹ ድል አደረጉ

ፈረሰኞቹ፣ ሐይቆቹ እና የጦና ንቦቹ ድል አደረጉ

በአብዩ አረጋሽ

ዛሬ በተደረጉ የ5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀዋሳ ከተማ እንዲሁም ወላይታ ዲቻ ድል ሲያስመዘግቡ ሲዳማ ቡናና መቻል ነጥብ ተጋሩ

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢትዮ ኤሌክትሪክን የገጠመው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቢላል ገመዳ ብቸኛ ግብ 1ለ0 በሆነ ውጤት ድል አድርጓል። በመጀመሪያው አጋማሽ በ37ኛው ደቂቃ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ናትናኤል ዳንኤል አክርሮ መቶት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ሲሆን በአጋማሹ ከተጠቀሰው አጋጣሚ ውጭ ይህ ነው የሚባል የግብ አጋጣሚ አልተፈጠረም። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያላደረገበት አጋማሽም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ የቢላል ገመዳ ተቀይሮ ወደ ሜዳ መግባት ለቅዱስ ጊዮርጊስ የተለየ የማጥሳት አማራጭ የሰጠው ሲሆን በ80ኛው ደቂቃም ቢላል ገመዳ ከእጅ ውርወራ የተገኘውን ኳስ በኢትዮ ኤሌክትሪክ የግብ ክልል ውስጥ ተቆጣጥሮ ወደ ግብነት በመቀየር ለቡድኑ ወሳኝ የድል ግብ አስቆጥሯል። በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ማስመዝገብ ችሏል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ጋሞ ጨንቻ

በቀን 9:00 ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ጋሞ ጨንቻን 2ለ1 በማሸነፍ ሶስት ነጥብ አግኝቷል።

ጨዋታውን በተሻለ መነቃቃት የጀመረው ጋሞ ጨንቻ በ15ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት መነሻው ያደረገውና የተጨራረፋውን ኳስ የትምጌታ ታደሰ ወደ ግብነት በመቀየር ቡድኑን መሪ አድርጓል። ግቧም ጋሞ ጨንቻ በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ከሜዳው ውጪ ያስቆጠራት የመጀመሪያ ግብ ሆና ተመዝግባለች።

ሀዋሳ ከተማ ከግቡ በኋላ ጫናውን በማሳደግ ወደ ጨዋታው የተመለሰ ሲሆን በ42ኛው ደቂቃ ብሩክ ከመሃል ሜዳ ይዞ የሄደውን ኳስ ወደ ሳጥን በማስገባት የፈጠረውን አጋጣሚ ቃልኪዳን ዘላለም ወደ ግብነት በመቀየር ሀዋሳን አቻ አድርጓል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ 1ለ1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ሀዋሳ ከተማ የበለጠ ጫና በመፍጠር ነበር የአሳድጓል። በ47ኛው ደቂቃም ብሩክ በየነ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በጥሩ ቦታ የነበረው ቃልኪዳን ዘላለም በማስቆጠር ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑም የድል ግብ በማስቆጠር ጨዋታውን 2ለ1 አድርጓል። በዚህም ሀዋሳ ከተማ ከመመራት ተነስቶ ድል ተቀዳጅቷል

ወላይታ ድቻ ከ ወልዋሎ ዓ/ዩ

በቀን 10:00 ሰዓት በሀላባ ኢንተርናሽናል ስታዲየም ወልዋሎን የገጠመው ወላይታ ድቻ 2ለ0 በሆነ ውጤት ድል አድርጓል። ጨዋታውን በተሻለ ብልጫ የጀመረው ወላይታ ድቻ በ27ኛው ደቂቃ በመሳይ ሰለሞን አማካኝነት የመጀመሪያ ግቡን አስቆጥሯል። የመጀመሪያውን አጋማሽ በጦና ንቦቹ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስም ወላይታ ድቻ ተጨማሪ ግቦች አስቆጥሮ መሪነቱን ለማስጠበቅ ጫና ማድረግ የቻለ ሲሆን በ70ኛው ደቂቃም ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ሀሰን ሁሴን ሁለተኛ ግብ በማስቆጠር መሪነቱን ወደ 2 ለ 0 አሳድጓል። ጨዋታው በዚህ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎም ወላይታ ድቻ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል።

ሲዳማ ቡና ከ መቻል

የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ምሽት 12:00 ሰዓት በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በሲዳማ ቡናና መቻል መካከል ተካሂዶ ያለ ግብ 0ለ0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የማጥቃት ፍላጎት በማሳየት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። መቻል በኳስ ቁጥጥር የተሻለ የነበረ ሲሆን ሲዳማ ቡና በፈጠራቸው የግብ አጋጣሚዎችና ሙከራዎች በኩል የተሻለ አደጋ መፍጠር ችሏል። ሆኖም የሁለቱም ቡድኖች ጥረት ወደ ግብነት ሳይቀየር አጋማሹ በ0ለ0 ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ በ62ኛው ደቂቃ የመቻሉ ተጫዋች ኮነህ ጄግባይ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ በማየቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። በዚህም መቻል የቀረውን የጨዋታ ጊዜ በ10 ተጫዋቾች ለመቀጠል ተገዷል።ሲዳማ ቡና የተጫዋች ብልጫውን ተጠቅሞ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ቢጥርም የመቻል ተጫዋቾች በቁጥር መቀነሳቸው ተጽዕኖ ሳያሳድርባቸው ተከላክለው አንድ ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል።