የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ5ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዶ ኢትዮጵያ መድን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3 ለ 1 በማሸነፍ ወደ ድል ተመልሷል።
በዐቢዩ አረጋሽ

በመጀመሪያው አጋማሽ ኢትዮጵያ መድን በግብ ቀዳሚ መሆን ችሏል። አልፍሬድ ኩሩንዚዛ ያቀበለውን ኳስ ሳሙኤል ሳሊሶ ወደ ግብነት በመቀየር መድንን 1 ለ 0 መሪ አድርጓል። ከግቡ በኋላ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቻ ለመሆን በርካታ ጥረቶችን ቢያደርግም የመጀመሪያው አጋማሽ በመድን መሪነት ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ንግድ ባንክ ጥሩ አጀማመር በማድረግ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢንቀሳቀስም በ58ኛው ደቂቃ የግብ ጠባቂውን ጊቢ ጆቤ ስህተት ዳዊት አውላቸው በመጠቀም ለኢትዮጵያ መድን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።
በ67ኛው ደቂቃ ወገኔ ገዛኸኝ ከአልፍሬድ ኩሩንዚዛ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ጠርዝ ላይ በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር የመድንን ሦስተኛ ግብ አስቆጥሯል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታውን ሳይተው መቀጠሉን በማሳየት በ83ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ኤርሚያስ ከቅጣት ምት እጅግ ድንቅ የሆነ ግብ በማስቆጠር የንግድ ባንክን ብቸኛ ግብ አስመዝግቧል። ሄኖክ ከቅጣት ምት ያስቆጠራት ድንቅ ግብ ከጨዋታው አስደናቂ ክስተቶች አንዷ ስትሆን በዘንድሮው የሊጉ ውድድር ለንግድ ባንክ ያስቆጠረውን ግብ ቁጥር ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል።

በመጨረሻም ጨዋታው በኢትዮጵያ መድን 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዚህ ውጤት ኢትዮጵያ መድን ከሽንፈት በኋላ በድጋሚ ወደ ድል ሲመለስ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት አስተናግዷል።
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ መድን የተፈጠሩለትን የግብ ዕድሎች በተሻለ ሁኔታ ወደ ግብነት በመቀየር የድሉ ባለቤት ሆኗል። በተቃራኒው ንግድ ባንክ በተከላካይ ክፍሉ የታዩትን ክፍተቶች ማረምና የጨዋታ ሚዛኑን መመለስ የሚጠበቅበት ይሆናል።

