መቻል አዲስ ቴክኖሎጂ በሊጉ ሊጠቀም ነው

መቻል አዲስ ቴክኖሎጂ በሊጉ ሊጠቀም ነው

መቻል የተጫዋቾቹን አካላዊ ብቃት በጨዋታ እና በልምምድ ወቅት የሚቆጣጠርበት አዲስ ቴክኖሎጂ መጠቀም ጀምሯል።

6ኛ ሳምንት ላይ በሚገኘው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 11 ነጥቦችን ይዞ በደረጃ ሰንጠረዡ 2ኛ ስፍራን የያዘው መቻል በክረምቱ ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ ቡድኑን በአዲስ መልክ እያደራጀ እንደነበረ አይዘነጋም። ራሱን ለማዘመን የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ የሚገኘው ክለቡ በዛሬው ዕለት ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መረጃ ቡድኑ በልምምድ ጊዜ እንዲሁም በጨዋታ ወቅት የተጫዋቾቹን አካላዊ ብቃት የሚለካበት አዲስ ቴክኖሎጂ አገልግሎት ላይ ማዋል ጀምሯል።

ስታትስፖርትስ ጂፒኤስ ቬስት የተባለው ይህ ቴክኖሎጂ ለዋናው የወንዶች ቡድን ግልጋሎት እንዲሰጥ የታሰበ ሲሆን እያንዳንዱ ተጫዋች ከማሊያው ስር አድርጎ ልምምድ እንዲሁም ጨዋታ ሲከውን የሚሸፍነውን የሜዳ ርቀት እንዲሁም የሚያወጣውን ፍጥነት አልፎም በእንቅስቃሴ ወቅት ያለበትን ጫና እና እየሸፈነ ያለውን የሜዳ ክፍል በግልፅ በቁጥሮች እና ምስሎች የሚያሳይ ይሆናል።

ሶከር ኢትዮጵያ እንዳገኘችው መረጃ ከሆነ ክለቡ ይህንን ቴክኖሎጂ ለ70 ተጫዋቾች የሚሆን ከነመቆጣጠሪያ ቁሶች ማስመጣቱ እና በዛሬው የልምምድ መርሐ ግብር ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። የፊታችን እሁድ ክለቡ ወደ ባህር ዳር አምርቶ ከባህር ዳር ከተማ ጋር በሚያደርገው ጨዋታም በይፋ በጨዋታዎች ወቅት መጠቀም እንደሚጀምር ተጠቁሟል።

ዓለም የደረሰባቸውን ቴክኖሎጂዎች ከመጠቀም የሚቦዝነው የሀገራችን እግርኳስ መሰል ነገሮችን መጠቀም መጀመሩ እጅግ የሚበረታታ ሲሆን ሌሎች ክለቦችም የመቻልን ተሞክሮ በመውሰድ ዘመኑ የደረሰባቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች መጠቀም ቢጀምሩ መልካም ነው።