በ2ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ትልቅ ግምት ያገኘው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት ጨዋታ በፈረሰኞቹ የበላይነት ተጠናቋል፡፡ በጨዋታው የታዩ ታክቲካዊ ጉዳዮችን ሶከር ኢትዮጵያ እንደተለመደው ይዛላችሁ ቀርባለች።
የመጀመሪያ አሰላለፍ
ደደቢት አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በሚታወቁበት የ4-4-2 ቅርፅ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ከሁለቱ የመሀል አማካዮች አስራት መገርሳ በተከላካይ አማካይነት እንዲሁም ሳምሶን ጥላሁን ከሳጥን እስከሳጥን አካሎ የመጫወቱን ሚና ይዘው ተጫውተዋል። የአስራት መገርሳ በመከላከል ጊዜ ብቻውን ከተከላካዮች ፊት መታየት እና ከሳምሶን በመጠኑ ወደፊት ከተጠጋ ሚና ጋር የቡድኑን አጨዋወት ወደ 4-1-3-2 የቀረበም እንዲመስል ሲያደርግ ነበር። ቡድኑ በመጀመሪያው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ካደረገው ጨዋታ በተለየ በግራ መስመር ላይ ኤፍሬም አሻሞን በሠለሞን ሀብቴ ምትክ ከመጠቀሙ በስተቀር በተመሳሳይ አሰላለፍ ነበር ቅዱስ ጊዮርጊስን የገጠመው።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጩ ጨዋታ ሶስት የተጨዋች ለውጥ ያደረገ ሲሆን የቡድኑ ቅርፅ ግን እንደተለመደው 4-3-3 ነበር። የፊት አጥቂው ሳልሀዲን ሰይድን በጉዳት ያጣው ጊዮርጊስ በቦታው አዳነ ግርማን ሲተካ በግራ መስመር ተከላካይነትም ዘካሪያስ ቱጂን በመሀሪ መና ለውጧል። የአስቻለው ታመነን አገልግሎት በቅጣት ምክንያት ማግኘት ያልቻለው የአሰልጣኝ ማርቲ ኖይ ቡድን በዚህ ጨዋታ ምንተስኖት አዳነን ከደጉ ደበበ ጋር በመሀል ተከላካይነት አጣምሯል (ደጉ በጉዳት ምክንያት በ30ኛው ደቂቃ ላይ በአይዛክ ኢዜንዴ ተቀየሮ ወጥቷል) ። በመሀል ሜዳ ላይም ጥሩ ቅንጅት እየታየባቸው ያሉትን ምንያህል ተሾመንን እና አብዱልከሪም ኒኪማን ከናትናኤል ዘለቀ ፊት ተጠቅሟል። ከአለም ዋንጫ ማጣረያ ጨዋታ መልስ ቡድኑን የተቀላቀለው ግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራም የቡድኑ ሌላው ለውጥ ነበር፡፡
ቡድኖቹ በወረቀት ላይ ሲታዩ
ሁለቱ ቡድኖች በንፅፅር ከሌሎቹ የሊጉ ክለቦች ይልቅ በሚያጠቁበት ወቅት በመስመር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው ጨዋታውን በበላይነት ለማጠናቀቅ ሚችለው ቡድን በመስመር ላይ ሚኖረውን ፉክክር በበላይነት ማጠናቀቅ ሚችለው እንደሆነ መገመት ይቻላል።
ደደቢት በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ በብዛት የማጥቃት ጨዋታው ከሽመክት ጉግሳ ቀኝ መስመር የሚነሳ ነበር ። የኤፍሬም አሻሞ በዚህ ጨዋታ በግራ መስመር መሰለፍ ቡድኑ በሁለቱም መስመሮች የተመጣጠነ ጥቃትን ለመሰንዘር የሚያስችለውን እድል የሚፈጥርለት ነበር። ከሁለቱ ክንፎች በተጨማሪ የፊት አጥቂዎቹ ጥምረት ቡድኑ ሚያገኛቸውን እድሎች ወደ ጎል ለመቀየር እና የተጋጣሚን ተከላካዮች ለመረበሽ የሚረዳ ሌላው የቡድኑ ጥንካሬ እንደሆነ መናገር ይቻላል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተረጋጋው የተከላካይ ክፍሉ በተጨማሪ የግብ ጠባቂው ሮበርት ኦዶንካራ መመለስ ከኃላ ያለውን ጥንካሬ የጨመረለት ሲሆን የምንያህል ተሾመ እና የአብዱልከሪም ኒኪማ ከመስመር አጥቂዎቹ ጋር ያለቻው ቅንጅት ጨዋታውን ለማሸነፍ የረዱት የቡድኑ ጥንካሬዎች ነበሩ። በበሀይሉ እና ባቡበከር ሚመራው የቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር ክፍል በተክለሰውነት እና የአየር ላይ ኳሶችን በመጠቀም ጥሩ ከሆነው አዳነ ግርማ የፊት አጥቂነት ጋር ሲጣመር ተሻጋሪ ኳሶችን ለመጠቀም ምቹ ያደርገዋል።
የመጀመሪያ አጋማሽ
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ የቅዱስ ጊዮርጊስ የበላይነት የታየበት ሆኖ አልፏል። የቡድኑ የበላይነትም መነሻ የነበረው በግራና በቀኝ መስመር የወሰደው ብልጫ ነበር። በጨዋታው መጀመሪያ ሁለቱም ቡድኖች በብዛት ለማጥቃት ይሞክሩ የነበረው በተመሳሳይ የሜዳው ክፍል ነበር ማለትም ቅዱስ ጊዮርጊስ በቀኝ መስመር በበሀይሉ አሰፋ አቅጣጫ እንዲሁም ደደቢት በግራ በኩል በኤፍሬም አሻሞ በኩል። የደደቢት የግራ መስመር ጥቃት ወደተጋጣሚው ሜዳ አልፎ ከመግባቱ በፊት በተደጋጋሚ ይቋረጥ ነበር። የመስመር ተከላካዩ ብርሀኑ ቦጋለ በማጥቃት ላይ የነበረው ተሳትፎ ማነስ እና የመሀል አማካዩ ሳምሶን ጥላሁን ጋር የነበራቸው ግንኙነትም በተጋጣሚያቸው የመሀል አማካዮች ብልጫ የተወሰደበት መሆኑ የግራ መስመሩን ጥቃት አቅም አሳጥቶት ነበር። ጊዮርጊሶችም በዚህኛው መስመር ከወሰዱትን ብልጫ በበሀይሉ እና በአብዱል ከሪም አማካይነት ይጎል እድሎችን ለመፍጠር ችለዋል።
የደደቢት የመጀመሪያ ሁለት ቅያሪዎችም የግራ መስመሩ ላይ ያተኮሩ ነበሩ። በ31ኛው ደቂቃ የግራ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ብርሀኑ ቦጋለ ወጥቶ ሰለሞን ሀብቴ ገብቷል። ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምርም ኤፍሬም አሻሞ በአቤል ያለው ተተክቷል። ከመጀመሪያው ቅያሪ በኃላ ደደቢቶች በግራ መስመራቸው በኩል የሚሰነዘርባቸውን ጥቃት ለመቀነስም ችለዋል ። ከዚህ ቅያሪ በኃላ የጊዮርጊስ ጥቃትም በብዛት አቡበከር ሳኒ ወደነበረበት የግራ መስመር በኩል ያጋደለ ሆኖ ተስተውሏል። ከወትሮው በተለየ ሁኔታም የቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች በሀይሉ እና አቡበከር በሙሉ ጨዋታው ቦታ ሳይቀያየሩ ጨርሰዋል፡፡ በጨዋታውም ቡድኑ በሚፈልገው መልኩ አንዲጫወት የሁለቱ ጠጨዋቾች ሚና ላቅ ያለ ነበረ፡፡
በሌላው የደደቢት መስመር ከወትሮው በተለየ ተፅእኖው ቀንሶ የነበረው ሽመክት ጉግሳም እንደኤፍሬም ሁሉ ከመስመር ተከላካዩ ስዩም ተስፋዬ በቂ እገዛ አላገኘም። የሚደርሱትን ኳሶችም በሱ አቅጣጫ ወደኃላ እየተሳበ ከሚመጣው አጥቂው ዳዊት ፍቃዱ ጋር እንዲሁም ከመሀል አማካዩ ሳምሶን ጋር ለመጫወት ሚያረገው ሙከራም ስኬታማ አልነበረም። ቡድኑ ወደግራ አድልቶ ማጥቃቱ ሽመክት ያለኳስ በእጅጉ ወደመሀል ተስቦ ሚገባባቸውን አጋጣሚዎችንም አሳይቶናል። ይህ ሂደትም በመከላከል ከተገደበው የቡድኑ የመስመር ተከላካዮች እንቅስቃሴ ጋር ተደምሮ የደደቢቶች ጥቃት ወደመሀል የጠበበ እንዲሆን አስገድዶታል። የመጀመሪያ የጎል ሙከራ ለማድረግም ደደቢቶች 38ኛው ደቂቃ ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው በመጀመሪያው ግማሽ ባጠቃላይም የግብ ሙከራ ማድረግ የቻሉት ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር።
ከሁለት የቆሙ ኳሶች መነሻነት በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦችን ያገኙት ቅ/ጊዮርጊሶች ከግቦቹ ውጪም ከሁለቱ መስመሮቻቸው መነሻነት ተደጋጋሚ እድሎችን መፍጠር ችለዋል። የተጋጣሚያቸውን የመስመር ጥቃት ማቆም ብቻም ሳይሆን የደደቢት የመስመር ተሰላፊዎች ከመሀል አማካዮቹ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማዳከም ችለዋል። የዚህን ብልጫ ምክንያቶች ከፋፍለን ስንመለከት በመጀመሪያ ሶስቱ የቡድኑ የፊት መስመር ተሰላፊዎች እንደሁልጊዜው የሜዳውን የጎን ስፋት በመጠቀም የነበራቸው አቋቋም ቡድኑ በየትኛው አጋጣሚ ወደማጥቃት ሲሸጋገር የሚኖረውን አማራጭ ስለሚያበዛው የደደቢት የመስመር ተከላካዮች ደፍረው ወደፊት በመሄድ ማጥቃቱን ለማገዝ እንዳይችሉ አግድዷቸዋል።
ሌላው እና ትኩረትን ሚስበው ጉዳይ የአጥቂ አማካዮቹ የምንያህል ተሾመ እና የአብዱልከሪም ኒኪማ ጥምረት ነው። በአርባምንጭ ጨዋታ ላይ የታየው የሁለቱ ተጨዋቾች በተጋጣሚ ሜዳ ላይ ያለኳስ የሚፈጥሩት ጫና ትናንትም የታየ ነበር። በተለይም የደደቢት የተከላካይ አማካይ አስራት መገርሳ እንዲሁም ሌሎቹ የቡድኑ የኃላ መስመር ተሰላፊዎች ኳስን በራሳቸው ሜዳ ላይ አደራጅተው ለመጀመር በሚያረጉት እንቅስቃሴ ወቅት የምንያህል እና የኒኪማ ኳስን በያዘው ተጨዋች ላይ የሚፈጥሩት ጫና (Ball oriented pressing በሚመስል ሁኔታ) ለቡድኑ የመጀመሪያ ግማሽ ብልጫ የጎላ ሚና ነበረው። ይህ ጫና በሁለቱ ተጨዋቾች ብቻ ሳይሆን በመስመር አጥቂዎቹ እና አልፎ አልፎም በተከላካይ አማካዩ ናትናኤል ዘለቀም አማካይነት ሚታገዝም ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ ከጫወታው መጠናቀቅ በኋላ ለምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸነገታ ባቀረበችው ጥያቄ ይህ አጨዋወት የታሰበበት እነደሆነ እና በቡድኑ እየተሞከራ እነደሆነ ገልፀዋል፡፡
ይህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጫና ለደደቢቱ ሳምሶን ጥላሁን ተፅእኖ መውረድም ዋናው ምክንያት ነው። ተጨዋቹ ከኳስ ጋር በሚገናኝበት ወቅት በምቾት ኳስን ለመስመር አማካዮቹም ሆነ ለፊት አጥቂዎቹ እንዳያሳልፍ የተጋጣሚው የመሀል ሜዳ ተሰላፊዎች ፈጣን የጎንዮሽ እና ቀጥተኛ ሩጫዎች ከፍተኛ ተፅእኖ ፈጥረውበት ነበር። ሳምሶን ያለኳስ በሚያረገውም እንቅስቃሴም በደደቢት ሜዳ ላይ በኒኪማ በቅዱስ ጊዮርጊስ አጋማሽ ደግሞ በናትናኤል አማካይነት በቅርበት በመያዙ የመስመር አማካዮቹ እሱን እንደተጨማሪ የማቀበያ አማራጭ እንዳይጠቀሙት አድርጓቸዋል። በዚህም መልኩ በመጀመሪያው አጋማሽ የደደቢቶች የማጥቃት አማራጮች በተጋጣሚያቸው ተዘግተው ሁለቱ አጥቂዎችም ከፊት ተነጥለው እና በቂ የጎል እድሎችን መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
የሁለተኛው አጋማሽ ለውጦች እና ውጤታቸው
በ2-0 መሪነት ሁለተኛውን አጋማሽ የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ውጤቱን በማስጠበቅ እንዲሁም በራሳቸው ሜዳ ላይ በመቆየት እና የሚያገኝዋቸውን እድሎች በመልሶ ማጥቃት ለመጠቀም በመሞከር ነበር ያሳለፉት። ቡድኑ በ79ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ አለባቸውን (21) በአብደሉከሪም ኒኪማ ቀይሮ በማስገባት የመሀል ሜዳውን የሶስት መዐዘን ቅርፅ ገልብጦታል። በዚህም ተስፋዬ ከናትናኤል ጎል በመሆን ለተከላካይ መስመሩ ተጨማሪ ሽፋን ሲሰጥ ከዚህኛው ቅያሪ 11 ደቂቃዎች በፊት በ68ኛው ደቂቃ ያስር ሙገርዋ (17) አቡበከር ሳኒን ቀይሮ በመግባት እንደተጠበቀው እና በአዲስ አበባ ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ ላይ ቡድኑ ኤሌክትሪክን ሲገጥም እንደታየው በመሀል አማካይነት ሳይሆን በአቡበከር የግራ መስመር አጥቂነት ቦታ ላይ ተተክቷል።
በጥቅሉ በዚህ አኳሀን ቅያሪዎችን ያረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው እጋማሽ በተጋጣሚው ሜዳ ላይ ያለ ኳስ ያረገው የነበረውን ጫና የቀነሰ ሲሆን አልፎ አልፎ ከታዩ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች እና በአዳነ አማካይነት ከተደረገች አንድ የግብ ሙከራ ውጪ በቀር በማጥቃቱ በኩል አስፈሪነቱ ቀንሶ ታይቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የነበረው እና በተስፋዬ መግባት ይበልጥ ክፍተቶችን መዝጋት የቻለው የተከላካይ ክፍሉም ከተጋጣሚው ከመጀመሪያው የበዛ የጎል ሙከራ ቢደረግበትም ግብ ሳያስተናግድ ለመውጣት ችሏል።
ደደቢቶች የተለየ የቅርፅ ለውጥ ባያረጉም ሁለት ጊዜ የተጨዋቾችን ቦታ አሸጋሽገዋል። በመጀመሪያ በሁለተኛው ግማሽ መጀመሪያ ላይ ኤፍሬም አሻሞን ቀይሮ የገባው አቤል ያለው (11) ፊት ላይ ከጌታነህ ጋር ሲጣመር ዳዊት ፍቃዱ ወደ ግራ መስመር መጥቶ ያይቷል። በመቀጠል ሌላው ሽግሽግ አኪሊሉ አየነው(14) በጨዋታው ተፅእኖ መፍጠር የተሳነውን ሳምሶን ጥላሁንን ተክቶ ሲገባ የታየ ነበር። በዚህም መሰረት አክሊሉ ከአይናለም ጎን የመሀል ተከላካይነቱን ሲይዝ በዚህ ቦታ ላይ የቆየው ኩሊባሊ ከደር ወደ መሀል አማካይነት በመውጣት የሳምሶንን ሚና ተረክቧል። ከዚህ ቅያሪ በኃላም በግራ መስመር ላይ እንዲጫወት የተደረገው ዳዊት ፍቃዱ ከ አቤል ጋር በመለዋወጥ ወደፊት አጥቂነቱ ተመልሷል።
በጨዋታው መጀመሪያ የቡድኑን የግራ ክፍል ይዘው የጀመሩትን ተጨዋቾችን በሂደት የቀየረው ደደቢት የሁለተኛውን አጋማሽ በብዛት በቀኝ መስመር በሚነሱ ኳሶች በመጠቀም ለማጥቃት ሞክሯል ጎል ባያስቆጥርም ከመጀመሪያው የተሻለ የግብ እድሎችንም ፈጥሯል። ነገር ግን የተጋጣሚውን የቀደመ ጫና መቀነስን ተከትሎ የሜዳውን የጎን ስፋት ለመጠቀም ያረገው ሙከራ አልነበረም። የግራ መስመር ላይ በተለያየ ጊዚያት ላይ የተተኩት ዳዊት እና አቤልም ወደቀኝ ባጋደለው የቡድኑ አጨዋወት በማሳብ ወደመሀል ይገቡ ነበር። የመስመር ተከላካዮቹ ሚናም ከጫናው መቀነስ በኃላም በማጥቃት ላይ የነበራቸው ፍላጎት አልታየም። በተለይ በግራ በኩል ለሰለሞን ይህን ለማረግ የሚያስችል ክፍተት በተደጋጋሚ ቢታይም ደደቢት እንደቡድን አጋጣሚውን ለመጥቀም ግን አልቻለም።
ምንአልባት ቡድኑ ላይ የታየው ለውጥ የቅርፅም ጭምር ቢሆን የተሻለ ነበር ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ከፊት ከነበሩት አጥቂዎች አንዱን በመቀነስ ከአስራት ጎን በቋሚነት የሚጫወት አማካይ ቢገባ የተሻለ ሽፋን ለተከላካዩ በመስጠት የመስመር አማካዮቹ ወደፊት ገፍተው እንዲጫወቱ እድል ቢፈጥርላቸው እንዲሁም ከሁለቱ አማካዮች ፊት ሚኖረው የአጥቂ አማካይም በተሻለ ነፃነት የተጋጣሚው ሜዳ ላይ እንዲገኝ ቢደረግ በሁለተኛው የጨዋታ ጊዜ የተሻለ ውጤት ያስገኝ ነበር ማለት ይቻላል።
በአጠቃላይ ጨዋታው በዚህ መልኩ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል። የኢትዮጽያ ፕሪምየር ሊግ ሶስተኛ ሳምንት በመጪው ሳምንት ቀጥሎ ሲካሄድ እሁድ ወልዲያ ላይ ደደቢት ወልዲያን በ9፡00 ሲገጥም ቅዱስ ጊዮርጊስ በአዲስ አበባ ስታድየም ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር በ 11፡30 የሚጫወት ይሆናል።