የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ ይካሄዳሉ፡፡ ዛሬ አንድ ጨዋታ ሲካሄድ በነገው እለት 7 ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡
ዛሬ በሚደረገው ብቸኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ፋሲል ከተማን 11:30 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ያስተናግዳል፡፡ ቡና በ2 ጨዋታ 1 ነጥብ ፤ ፋሲል ከ1 ጨዋታ 0 ነጥበ እንደመያዛቸው የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል ለማስመዝገብ አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡
ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻ አዳማ ከተማን እሁድ 09:00 ላይ የሚያስተናድበት ጨዋታ ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች አንዱ ነው፡፡ አዳማ ከ2 ጨዋታ 6 ነጥብ ሰብስቦ ወደ ሶዶ ሲያቀና ከፋሲል ከተማ ጋር የነበረው ጨዋታ ወደ ሌላ ቀን በመተላለፉ ሳምንቱን ያለ ጨዋታ ያሳለፈው ወላይታ ድቻ የ1ኛ ሳምንት ድሉን ለመድገም ይፋለማል፡፡
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዘመኑ የመጀመርያ የሜዳ ጨዋታው ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር 09:00 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይጫወታል፡፡ ኤሌክትሪክ ባደረጋቸው 2 የሜዳ ውጪ ጨዋታዎች 1 ነጥብ ብቻ የያዘ ሲሆን አዲሱ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ አአ ከተማ 4 ነጥብ በመሰብሰብ ጥሩ አጀማመር አድርጓል፡፡
ሲዳማ ቡና ይርጋለም ላይ ድሬዳዋ ከተማን ያስተናግዳል፡፡ አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ፣ ተጫዋቾቹ አሳምነው አንጀሎ እና ዘነበ ከበደ ወደ ቀድሞ ክለባቸው ሜዳ ተመልሰው የሚያደርጉት የመጀመርያ ጨዋታ ይሆናል፡፡
መልካ ቆሌ ላይ ወልድያ ደደቢትን 09:00 ላይ ያስተናግዳል፡፡ ወልድያ 4 ነጥብ በመያዝ ጥሩ አጀማመር ሲያደርግ በተከታታይ ፈታኝ ጨዋታዎች የገጠመው ደደቢትም በአንድ አሸንፎ እና በሌላኛው ተሸንፎ መጥፎ ያልሆነ አጀማመር አድርጓል፡፡
ሀዋሳ ላይ ሀዋሳ ከተማ አርባምንጭ ከተማን ያስተናግዳል፡፡ በክብረአብ ዳዊት ህልፈት ምክንያት በሀዘን ድባብ የተዋጡት ሀዋሳዎች ከ1 ሳምንት እረፍት በኃላ የውድድር ዘመኑን የመጀመርያ ድል በማስመዝገብ ክብረአብን ለመዘከር ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡ ከ2 ጨዋታ 1 ነጥብ ብቻ ያስመዘገበው አርባምንጭም የመጀመርያ 3 ነጥቡን ለማግኘት ጠንካራ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጅማ አባ ቡና በታሪክ የመጀመርያ ድሉን እና ግቡን ለማግኘት በማለም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጅማ ላይ ያስተናግዳል፡፡ ጅማ ሁለቱም ጨዋታ ያለግብ ሲያጠናቅቅ ንግድ ባንክ ባደረገው አንድ ጨዋታ ሽንፈት አስተናገዷል፡፡
በ3ኛው ሳምንት የመጨረሻ መርሃ ግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ መከላከያ አመሻሽ 11:30 ላይ በአዲስ አበባ ስታድየም ይፋለማሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ6 ነጥብ የሊጉ መሪ ሲሆን መከላከያ ከ2 ጨዋታ 1 ነጥብ በመያዝ ከወገብ በታች ይገኛል፡፡