የሴቶች ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት | ደደቢት እና ንግድ ባንክ መሪነታቸውን ቀጥለዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከእሁድ ጀምሮ ተካሂደው ዛሬ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል፡፡ ደደቢት ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሸናፊነታቸው ሲቀጥሉ ቤዛዊት ንጉሴ የሳምንቱ ክስተት ሆናለች፡፡

ምድብ ሀ

አዳማ ከተማ በጥሩ አቋሙ ዘልቋል፡፡ እሁድ ወደ ድሬዳዋ ተጉዞ ድሬዳዋ ከተማን 1-0 በማሸነፍ 2ኛ ደረጃውን አጠናክሯል፡፡ አዳማ ዘንድሮ እጅግ መሻሻል ካሳዩ ቡድኖች ግንባር ቀደሙ ሲሆን ከ7 ጨዋታዎች በስድስቱ ሙሉ 3 ነጥቦች መሰበሰብ ችሏል፡፡

እሁድ በሸገር ደርቢ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጫወታቸው ቀደም ብሎ 08:00 ላይ በተደረገ ጨዋታ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ንፋስ ስልክን 1-0 አሸንፏል፡፡

ትላንት በአዲስ አበባ ስታድየም 2 ጨዋታዎች ተካሂደዋል፡፡ 09:00 ላይ በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ጥረት 1-1 አቻ ተለያይተዋል፡፡ 11:30 ላይ ደግሞ ቦሌ ክፍለ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡

በሳምንቱ ከተካሄዱት ጨዋታዎች መካከል ደደቢት ከመከላከያ በአበበ ቢቂላ ያደረጉት ጨዋታ ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ ነበር፡፡ ማክሰኞ 09:00 ላይ የተደረገውን ጨዋታ ደደቢት በሎዛ አበራ እና መስከረም ካንኮ ግቦች ታግዞ 2-1 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ድሉን ተከትሎ ሰማያዊዎቹ ከ7 ጨዋታ ሙሉ 21 ነጥቦች በመሰብሰብ ምድቡን መምራታቸውን ቀጥለዋል፡፡

ቀጣይ ጨዋታዎች (8ኛ ሳምንት)

ቅዳሜ ታህሳስ 29 ቀን 2009

09:00 ደደቢት ከ ኢ.ወ.ስ. አካዳሚ (አአ ስታድየም)

11:30 ኢት. ቡና ከ ንፋስ ስልክ ላፍቶ (አአ ስታድየም)

እሁድ ታህሳስ 30 ቀን 2009

09:00 ጥረት ከ ቦሌ ክ/ከተማ (ባህርዳር)

09:00 አዳማ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ (አዳማ)

ሰኞ ጥር 1 ቀን 2009

09:00 መከላከያ ከ ድሬዳዋ ከተማ (አአ ስታድየም)


ምድብ ለ

የምድብ ለ እሁድ በተደረገው የሲዳማ ቡና እና አርባምንጭ ጨዋታ ነበር የተጀመረው፡፡ ይርጋለም ላይ የተደረገው ጨዋታ በሲዳማ ቡና 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ዛሬ በዚህ ምድብ 4 ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ ሀዋሳ ከተማ ቅዱስ ጊዮርጊስን አስተናግዶ 3-1 በማሸነፍ ንግድ ባንክን መከተሉን ቀጥሏል፡፡ አይናለም አሳምነው ፣ ትርሲት መገርሳ እና ስንታየሁ መንግስቱ የሀዋሳን የድል ግቦች ሲያስቆጥሩ ሜሮን አብዶ የፈረሰኞቹን ብቸኛ ግብ አስቆጥራለች፡፡

ዲላ ላይ ልደታን ያስተናገደው ጌዲኦ ዲላ 3-2 በመርታት ተከታታይ 2ኛ ድሉን ማስመዝገብ ችሏል፡፡

09:00 ላይ በአዲሰ አበባ ስታድየም አቃቂ ቃሊቲ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲን 3-1 አሸንፏል፡፡ በስፍራው የነበረውን ተመልካች ያዝናና እንቅስቃሴ በታየበት በዚህ ጨዋታ ቤዛዊት ንጉሴ 3ቱንም የአቃቂ ቃሊቲ ግቦች በማስቆጠር ሐት-ትሪክ ሰርታለች፡፡ ቤዛዊት ግቦቹን ያስቆጠረችበት መንገድ እና ያላት ክህሎት የወደፊቱ የኢትዮጵያ ሴቶች እግርኳስ ኮከብ እንደምትሆን ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ ከቤዛዊት በተጨማሪ የአጥቂ አማካይዋ ንግስት ኃይሉ እንቅስቃሴ አስደናቂ ነበር፡፡

የ8ኛው ሳምንት መርሃ ግብር ፍጻሜውን ያገኘው 11:30 ላይ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አዲስ አበባ ከተማን ባገናኘው ፍልሚያ ነው፡፡ በሴቶች እግርኳስ ትልቅ ስም ያላቸው አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እና አስራት አባተን ያገናኘው ጨዋታ በብርሃኑ ግዛው ንግድ ባንክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ጨዋታውን የመራችው ዳኛ የመጀመርያው ግማሽ ሳይጠናቀቅ ፊሽካ በመንፋት ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል በማምራት ላይ ሳሉ በድጋሚ በመጥራት ጨዋታውን እንዲቀጥል ማድረጋቸው አስገራሚ ሆኗል፡፡

ቀጣይ ጨዋታዎች (8ኛ ሳምንት)

እሁድ ታህሳስ 30 ቀን 2009

09:00 ልደታ ክ/ከተማ ከ ኢት. ን. ባንክ (አአ ስታድየም)

11:30 ቅድስት ማርያም ከ አአ ከተማ (አአ ስታድየም)

ሰኞ ጥር 1 ቀን 2009

11:30 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አቃቂ ቃሊቲ (አአ ስታድየም)

ቅዳሜ ጥር 6 ቀን 2009

09:00 አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ (አርባምንጭ)

09:00 ጌዲኦ ዲላ ከ ሲዳማ ቡና (ዲላ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *