ሽመልስ በቀለ ስለ አል አህሊ ዝውውሩ ፣ ጉዳት እና ወቅታዊ አቋሙ ይናገራል

የዋልያዎቹ እና የፔትሮጄት ኮከብ ሽመልስ በቀለ በግብጽ አስደሳች ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል፡፡ የግብጽ ፕሪምየር ሊግ 2ኛ ዙር የውድድር ዘመን እስኪጀምር የእረፍት ጊዜውን ሀገር ቤት በማሳለፍ ላይ የሚገኘው ሽመልስ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ስለ ውድድር ዘመኑ

ሊጉ (ግብፅ) ከአመት አመት አመት ውድድሩ እየጠነከረ ነው፡፡ አሁንም የአል አህሊና የዛማሌክ የበላይነት እንዳለ ሆኖ ሌሎች ክለቦች በፋይናንስም ፣ በሚያስፈርሟቸው የተጨዋቾች ጥራት የተነሳ ውድድሩ ጠንካራ ፉክክር እየታየበት ይገኛል።

የክለቡ ወጥ ያልሆነ አቋም

እንቅስቃሴያችን ብዙ የሚያስከፋ አይደለም ጥሩ ነው ። ተጨዋቾቹ አሰልጣኙ የሚሰጣቸውን መመርያ የሚተገብሩ ናቸው። በዚህ 17 ጨዋታ የመጀመርያዎቹ ሳምንታት አጀማመራችን ጥሩ ነበር፡፡ ወደ መጨረሻ ስድስት ሳምንት ጨዋታዎች ግን ጥሩ አልነበርንም ፤ ተዳክመን ነበር። በዚህ ላይ የገጠምናቸው ቡድኖች ጠንካራ ከመሆናቸው ጋር ተደምሮ ውጤታችን ወርዷል። በሁለተኛው ዙር እናስተካክላለን ብዬ አስባለው።

የግል አቋም

በአጨዋወቴ ግብፃውያን እንደሚደሰቱ አውቃለው ፤ ጎልም እያስቆጠርኩ ነው። ይመስለኛል ይህ የሆነው አሰልጣኛችን የሚሰጠኝ የጨዋታ ነፃነት ይመስለኛል፡፡ እኔም ከዚህ በፊት ሀዋሳ ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በነበረኝ ቆይታ የነበሩት አሰልጣኞች ይሰጡኝ በነበረው ነፃነት ነው ጥሩ እንቀሳቀስ የነበረው ። የፔትሮጄት አሰልጣኝም ነፃነት ሰጥቶኝ በመጫወቴ ጎል ማስቆጠሬና እና ጥሩ መሆኔ ከዛ የመጣ ይመስለኛል። ከዚህም በኋላ የተቻለኝን በማድረግ ጎል የማግባት አቅሜን መጨመር እፈልጋለው፡፡

በቅርቡ ስላጋጠመው ጉዳት

እግሬ ላይ በደረሰ ጉዳት የተወሰኑ ጨዋታዎች አልነበርኩም፡፡ አሁን የመጀመርያው ዙር የግብፅ ሊግ ተጠናቆ የዕረፍት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ 15 ቀን ለእረፍት በሀገሬ በነበረኝ ቆይታ እግሬን እየታሸው ነበር ፤ አሁን የጤናዬ ሁኔታ መሻሻል እያሳየ ይገኛል፡፡ ዛሬ ወደ ካይሮ አቀናለው ልምምዴንም በሚገባ እሰራለው ።

በአል አህሊ ስለመፈለጉ 

ያው አንተ እንደምትነግረኝ ብዙ ወሬዎች አሉ፡፡ እኔ ተጨዋች ነኝ ፤ እስካሁን ድረስ ክለቤን እያገለገልኩ እገኛለው፡፡ ጥሩ በተጫወትክ መጠን ብዙ ቡድኖች ይፈልጉሀል፡፡ አሁን የጥር ወር የዝውውር መስኮት በመከፈቱ ድንገት አል ሀሊኢዎች እኔን ፈልገውኝ ይሆናል ፤ በርግጥ እኔ አላቅም፡፡ ከኤጀንቴ ጋር ተነጋግረው ይሆናል፡፡ አሁን ላይ ምንም ማለት አልችልም፡፡ እዛ ሄጄ ስነጋገርና ስፈርም ነው እርግጠኛ የምሆነው።

የፔትሮጄት ውሉ እክል ይፈጥርበታል?

በርግጥ አሁን ካለሁበት ክለብ ጋር ውሌን ያደስኩት ዘንድሮ ነው ። ይህም መሆኑ የሚያጨናግፍብኝ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ከክለቤ ጋር ያለኝ መልካም ግኑኝነት አንፃር ክለቡም የተሻለ ነገር ስለሚያገኝ እኔም ወደ ተሻለ ነገር ስለምሄድ ዝውውሩ ይቀበሉታል ብዬ አስባለው ።

ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ

ባለሁበት ቦታ ሆኜ በድረ-ገፆች በተለይ በእናንተ ድረ-ገፅ ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ እከታተላለው፡፡ በተለያየለ ምክንያቶች በምመጣበት አጋጣሚም እመለከታለው፡፡ በፊት ከነበረው ሳነፃፅረው በጣም ኳስ የሚችሉ ተጨዋቾች አይቻለው፡፡ ልምምዳቸውንና በሚገባ ከሰሩ አይምሮአቸውን ለጨዋታ ካዘጋጁ የተሻለ ደረጃ መድረስ ይችላሉ። ካየሁት አንፃር የታዘብኩት የልምምድ እና የአሰለጣጠን ችግር ይመስለኛል ሜዳ ላይ አንዳንዴ መደረግ የሌለባቸው ሲያደረጉ አያለው ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *