የጋቦን 2017 ተሳታፊዎች ፕሮፋይል | ጋና ብሄራዊ ቡድን [ብላክ ስታርስ]

የቶታል 2017 አፍሪካ ዋንጫ በጋቦን አዘጋጅነት ቅዳሜ ይጀመራል፡፡ ዋንጫውን ለማንሳት ቅድመ ግምቱን ካገኙ ሃገራት መካከል ምዕራብ አፍሪካዊቷ ጋና ተጠቃሽ ናት፡፡ 

ብላክ ስታርስ በሚል ተቀፅላ ስም የሚታወቁት ጋናዎች ከ2008 የአፍሪካ ዋንጫ አንስቶ ለአምስት ተከታታይ ግዜያት የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚዎች ነበሩ፡፡

 

የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ብዛት – 21

ተጠቃሽ ውጤት፡ አራት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮን (1963፣ 1965፣ 1978 እና 1982)

አሰልጣኝ፡ አቭራም ግራንት

ጋና በምድብ አራት ከማሊ፣ ግብፅ እና ዩጋንዳ ጋር ተደልድላለች፡፡ ብሄረዊ ቡድኑ ከአፍሪካ ዋንጫ በፊት የአቋም መለኪያ ጨዋታ በሚፈለገው መጠን አለማግኘቱ እንደድክመት ቢቆጠርም እስራኤላዊው አሰልጣኝ ግራንት በጋና የሚኖራቸው ቆይታ በጋቦን በሚመዘገበው ውጤት ይወሰናል፡፡

ለጋናው Ghansoccernet.com እና አዴሄ 99.1 ኤፍኤም የሚሰራው የእግርኳስ ጋዜጠኛው ኑሁ አዳምስ ስለሃገሩ ጋና የአፍሪካ ዋንጫ የሚከተለውን አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥቷል፡፡

 

ስለምድብ አራት

“እውነት ለመናገር ምድብ አራት ከባድ ከሆኑት የአፍሪካ ዋንጫ ምድቦች መካከል ይመደባል፡፡ ምክንያቱም የምንግዜም ባለሪከርዷን ግብፅ ምንም እንኳን ላለፉት ሶስት ውድድሮች ባትሳተፍም በምድቡ ትገኛለች፡፡ በማጣሪያው ጠንካራ እንደነበሩ ማየት ይቻላል፡፡ ማሊ ሌላኛው ጠንካራ ሃገር ናት፡፡ ሁሌም ጋናን ሲገጥሙ ለመሻሻል ጥረት የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ጋናን በደረጃ ጨዋታ አሸንፈው ያውቃሉ፤ ጋና በምድብ ጨዋታ ብታሸንፍም፡፡ ዩጋንዳ ከ39 ዓመታት በኃላ ነው የምትሳተፈው፡፡ የመጨረሻ የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታቸው ከጋና ጋር በ1978 ነበር፡፡ የማጣሪያ ዙሩን ተንተርሰን ዩጋንዳ ከፍተኛ መሻሻልን ያሳየች ሃገር ናት፡፡ ጋና የካበተ ልምድ ስላላት ከምድቡ ለማለፍ አትቸገርም፡፡ እኔ ጥሩ ተስፋ አለኝ ከምድብ እንደምናልፍ፡፡”

 

ስጋት

“የጋና ችግር ዋንጫ አለማንሳት ነው፡፡ እኔ ይህንን ከዕድል ጋር አያይዘዋለው፡፡ ከ2008 ጀምሮ በአፍሪካ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ነበርን፡፡ ይህ ጥሩ የሆነ ማሳያ ነው ዋንጫ ላለማንሳታችን ዕድለኛ ስልነበርን ነው፡፡”

 

የዋንጫ ተስፋ

“የ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የማንሳት ተስፋችን ላቅ ያለ ነው፡፡ በቅርብ ግዜያት ያሳየነው መጥፎ እንቅስቃሴ ቢኖርም እስከግማሽ ፍፃሜ መጓዝ እንችላለን፡፡ ይህ ለጋና የአፍሪካ ዋንጫ ለማንሳት ትክክለኛው ግዜ ነው፡፡”

 

የተጫዋቾች ስብስብ

ጋና የብሄራዊ ቡድን ስብስቧ ጠንካራ ነው፡፡ በሁሉም ክፍሎች ጥራት ያለቸውን ተጫዋቾች ይዛለች፡፡ ቢሆንም የአስሞሃ ጂያን ያክል ተፅዕኖ መፍጠር የሚችል ተጨዋች ለማግኘት ትቸገራለች፡፡ ጂያን ከግብ ማስቆጠሩ ባሻገር ቡድኑን በመመራት ይታወቃል፡፡ ለአፍሪካ ዋንው ብዙም እንግዳ ላለሆነው የአል አሃሊ ክለብ ዱባዩ አጥቂ ለተጋጣሚ ቡድኖች ፈተና እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ የተጋጣሚን የተከላካይ ስፍራ በመረበሽ እንዲሁም ኳስን ይዞ መጫወት የሚችለው የቀድሞ የጋና ኮከብ የአቢዲ አዩ ልጅ አንድሬ በጋና በኩል ከሚጠበቁ ተጫዋቾች መካከል ነው፡፡ ጋና ከሁለቱ ባሻገር እንደ ክሪስቲያ አትሱ፣ ቶማስ ፓርቴ፣ ኢማኑኤል ባዱ፣ አብዱልራህማን ባባ እና የመሳሰሉት ይዟል፡፡ ብሄረዊ ቡድን ከሃገር ውስጥ አንድ ብቻ ተጫዋችን ያካተተ ሲሆን ብዙውን ግዜ በጋና ከማያሳለፉት ግራንት የሚጠበቅ ምርጫ ነው፡፡ የጋና ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን ዋ ኦል ስታርስ ተጫዋች ብቸኛው የሃገር ውስጥ ክለብ ነው፡፡

 

የማጣሪያ ጉዞ

ጋና በምድብ ስምንት ከሩዋንዳ፣ ሞዛምቢክ እና ሞሪሺየስ ጋር ነበር የተደለደለችው፡፡ ምድቡ በመሪነት ያጠናቀቁት ብላክ ስታርሶች በስድስት የማጣሪያ ጨዋታዎቸ አራት አሸንፈው በሁለት ጨዋታዎች አቻ ወጥተው ነበር ወደ ጋቦን ያቀኑት፡፡

ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

ራዛክ ብሪማ (ኮርዶባ/ስፔን)፣ ሪቻርድ ኦፎሪ (ዋ ኦል ስታርስ/ጋና)፣ ፋቱ ዳዉዳ (ኢኒየምባ/ናይጄሪያ)

ተከላካዮች

ጆናታን ሜንሳህ (ኮሎምበስ ክሩ/ዩናይትድ ስቴትስ)፣ አብዱልራህማን ባባ (ሻልክ04/ጀርመን)፣ ዳንኤል አማርቴ (ሌስተር ሲቲ/እንግሊዝ) ኤድዊን ጂማ (ኦርላንዶ ፓይሬትስ/ደቡብ አፍሪካ)፣ ጆን ቦይ (ሲቫስፖር/ቱርክ)፣ ሃሪሰን አፉል (ኮሎምበስ ክሩ/ዩናይትድ ስቴትስ)፣ ኢማኑኤል ባዱ (ዩድኔዜ/ጣሊያን)

አማካዮች

አንድሪው ካየር-ያዶም (በርንስሌ/እንግሊዝ)፣ ቶማስ ፓርቴ (አትሌቲኮ ማድሪድ/ስፔን)፣ አፍሪ አኩዋ (ቶሪኖ/ጣሊያን)፣ ክሪስቲያን አትሱ (ኒውካስል ዩናይትድ/እንግሊዝ)፣ ሙባረክ ዋካሶ (ፓናቲኒያኮስ/ግሪክ)፣ ኢቤኒዜር ኦፎሪ (ኤአይኬ/ስዊድን)፣ ሳሙኤል ቲቴ(ላይፈሪንግ/ኦስትሪያ)

አጥቂዎች

ጂያን አሰሞሃ (አል አሃሊ/የተባበሩት የአረብ ኤምሬቶች)፣ ጆርዳን አዩ (አስቶንቪላ/እንግሊዝ)፣ ኢቤኔዘር አሲፏ (ሲዮን/ስዊዘርላንድ)፣ በርናርድ ቴክፒቲ (ሻልክ 04/ጀርመን)፣ ፍራንክ አቼምፖንግ (አንደርሌክት/ቤልጂየም)፣ አንድሬ አዩ (ዌስትሃም ዩናይትድ/እንግሊዝ)

 

ጋና የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ዩጋንዳን በዕለት ማክሰኞ በመግጠም ትጀምራለች፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *