ሪፖርት | አዝናኙ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

በድሬዳዋ ከተማ ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ቀትር ላይ ወልቂጤ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ያገናኘው እና በሁለቱ አጋማሾች ሁለት መልኮች የነበሩት ጨዋታ ሁለት አቻ ተጠናቋል።

ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ በቁጥር በርከት ብለው መሀል ሜዳው ለመቆጣጠር እና ወልቂጤ ከተማን ጫን ብለው የመጫወት ፍላጎት የነበራቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎችን በአመዛኙ በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ቢያሳልፉም ተስፋዬ አለባቸው ከርቀት ከሳጥን ውጪ ካደረጋቸው ሙከራዎች ውጪ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቢቀሩም በ15ኛው ደቂቃ ግን መሪ የሆኑባትን ጎል ማግኘት ችለዋል።

ቀጣዩ የሆሳዕናዎች ሙከራ ግን ወደ ግብነት የተለወጠ ነበር። ተስፋዬ አለባቸው ከመሀል ሜዳ አካባቢ ተከላካዮች ጀርባ ያደረሰውን ኳስ የቀኝ መስመር ተመላላሹ ብርሃኑ በቀለ ከቀኝ መስመር ሰብሮ ወደ ውስጥ ካጠበበ በኋላ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ፍቅረየሱስ ተ/ብርሃን 15ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም አጨራረስ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ነገርግን በ25ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ሳይጠበቅ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላካት ኳስ የግቡ አግዳሚን ለትማ ስትመለስ በቅርብ ርቀት የነበረው ጫላ ተሺታ በግንባሩ በመግጨት ቡድኑን አቻ አድርጓል። ከግቦቹ በኋላ ተነቃቅቶ በቀጠለው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠራቸውን ሲቀጥሉ ሀዲያ ሆሳዕናዎች አንፃራዊ የበላይነታቸውን ማስቀጠል ችለዋል።

ክፍት ሆኖ በቀጠለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ33ኛው ደቂቃ ላይ ሰዒድ ሀብታሙ የሰራውን የማቀበል ስህተት ተከትሎ ብርሃኑ በቀለ ያገኘውን ኳስ አስቆጠረው ተብሎ ሲጠበቅ ያመከነው በጣም አስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በ41ኛው ደቂቃ ግን ሆሳዕናዎች ተመልሰው መሪ መሆን ችለዋል ፤ ሆሳዕናዎች በግሩም ቅብብል የሄዱትን ኳስ በወልቂጤ ከተማ ተጫዋቾች የቦታ አያያዝ ስህተት ታግዞ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ባዬ ገዛኸኝ በግሩም አጨራረስ የቡድኑን ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።

ኳስን የመቆጣጠር ውጥናቸው ያልሰመረላቸው ወልቂጤዎች በሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው ሁሉ የሀዲያ ሆሳዕናዎች የመስመር ተመላላሾችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ተቸግረው ተስተውሏል።

በሂደት ግን ወልቂጤ ከተማዎች ሆሳዕናዎች ጨዋታውን የጀመሩበትን መንገድ ማስቀጠል አለመቻላቸውን ተከትሎ በጨዋታው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን በመውሰድ ሙከራዎችን በተደጋጋሚ ማድረግ ጀምረዋል። ጌታነህ ከበደ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እንዲሁም በ67ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር ረመዳን የሱፍ ወደ መሀል ያሳለፈለትን ኳስ ሳጥን ውስጥ የነበረው አህመድ ሁሴን በኩል ያደረጓቸውን አስደናቂ ሙከራዎቹ በሆሳዕናው ግብ ጠባቂ ሶሆሆ ሜንሳ ሊመክንባቸው ችሏል።

በአጋማሹ በሀብታሙ ታደሰ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ የመታት እና ሀብታሙ ካዳነበት ኳስ ውጭ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ የተቸገሩት እና ብልጫ የተወሰደባቸው ሆሳዕናዎች ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት ቢቃረቡም በ89ኛው ደቂቃ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አላዛር ዘዉዱ ባስቆጠራት ግብ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ወልቂጤ ከተማዎች በ16 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ በ13 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉችለዋል።