አዲሱ የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ላንት ምሽት አዲስ አበባ ገብተው የተለያዩ ክንውኖችን በማከናወን ዛሬ ረፋድ ላይ ኢትዮጵያን ለቀዋል፡፡
ኢንፋንቲኖ ትላንት በደቡብ ሱዳን ጁባ በነበራቸው የጥቂት ሰአታት ቆይታ የደቡብ ሱዳን እና ቤኑን ጨዋታን ተመልክተው እንዲሁም በፊፋ ድጋፍ የተሰራው የሃገሪቱ እግርኳስ ፌዴሬሽን ህንፃን በመመረቅ ካሳለፉ በኋላ ምሽት 2፡30 ገደማ አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
በፊፋ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት የድምፅ ቆጠራ ላይ ተሳትፎ ያደረጉት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢንፋንቲኖ ወደ ሃገራችን መምጣት ምክንያት ያስረዳሉ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ እግርኳስን በቀደምትነት ከመሰረቱ ሀገሮች አንዷ በመሆኗ ፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጨ በመሆኗ ፣ የእግርኳስ መሰረተ ልማቶች በማስፋፋት ላይ የምትገኝ በመሆኗ እና በፊፋ ምርጫ ወቅት በነበረን ተሳትፎ ምክንያት እንዲሁም ከእኛ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት ነበር የመጡት፡፡›› ይላሉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ አክለውም በተደረገላቸው አቀባበል እና በቆይታቸው ደስተና መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
‹‹ በአቀባበላችን ባደረግንላቸው መስተንግዶ በጣም ደስተኛ ነበሩ፡፡ ባረፉበት ሸራተን አዲስ ልደታቸውን አክብረንላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ በነበራቸው አጭር ቆይታ በጣም ደስተኛ ነበሩ፡፡›› ብለዋል፡፡
ጂያኒ ኢንፋንቲኖ በቆይታቸው ፌዴሬሽኑ ያሰባቸውን ነገሮች መከወኑንና ቆይታቸው የተሳካ እንደነበር ገልፀዋል፡፡
‹‹ ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ካረጋገጥንበት እለት ጀምሮ በደንብ ተዘጋጅተን የጠበቅናቸው በመሆኑ በሊግ አወቃቀር ፣ በታዳጊዎች ልማት እና ሌሎች ወደ 9 በሚጠጉ ጉዳዮች ዙርያ ውይይት አድርገናል፡፡ በአቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲያደርጉልን ውይይት ያደረግን ሲሆን እርሳቸውም ለኢትዮጵያ እግርኳስ የነበራቸው ግምት እንደተቀየረና ድጋፍ እንደሚያደርጉም አሳውቀዋል፡፡
‹‹ ጉብኝታቸው እጅግ የተሳካ ነበር፡፡ ፊፋ ድጋፍ እንዲያደርግልን በምንፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገናል፡፡ እርሳቸውም ድጋፍ እንደሚያደርጉ በመግለጽ ከወራት በኋላ በድጋሚ ተመልሰው እንደሚመጡ ቃል ገብተውልናል፡፡ ››
የ46 አመቱ ጂያኒ ኢንፋንቲኖ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ትላንት ምሽት ከወጣቶች እና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ጋር የተወያዩ ሲሆን ባረፉበት ሸራተን አዲስ የእራት ግብዣ ተደርጎላቸዋል፡፡ የተዘጋጀላቸውን ልዩ ኬክ በመቁረስም የ46ኛ አመት የልደት በአላቸውን አክብረዋል፡፡
ዛሬ ጠዋት ደግሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽህፈት ቤት እና የወጣቶች ስፖርት አካዳሚን የጎበኙ ሲሆን በዚህ አመት መጨረሻ ተመልሰው በመምጣት ኢትዮጵያን በስፋት ለመቆብኘት እንዳቀዱ በመግለፅ ረፋድ 4፡00 ገደማ ኢትዮጵያን ለቀዋል፡፡