ሪፖርት | ሽረ እና ፈረሰኞቹ አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | ሽረ እና ፈረሰኞቹ አቻ ተለያይተዋል

የስታዲየም መብራት በመጥፋቱ ምክንያት 90ኛው ደቂቃ ላይ ተቋርጦ ዛሬ ለ6 ደቂቃዎች ያህል የተደረገው የምድረገነት ሽረ እና የፈረሰኞቹ ጨዋታ 0ለ0 ተጠናቋል።

በአዳማ ከተማ የተደረገው ሁለተኛው ጨዋታ ምድረገነት ሽረን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያገናኘ ሲሆን በመጀመሪያ አጋማሽ እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራዎች ባይደረጉም ከተከላካይ ጀርባ የተጣለውን ኳስ ዳንኤል ዳርጌ አግኝቶ ግብ ጠባቂው በሸፈነበት አንግል መትቶ ለጥቂት የወጣባቸው የሽረዎች ቀዳሚው ሙከራ እንዲሁም ቢነያም ላንቃሞ ከሳጥን ውጭ አክርሮ መትቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረባቸው ሙከራዎች የተሻሉ ነበሩ።

ፈረሰኞቹ በበኩላቸው አልፎ አልፎ ወደ ሳጥን ሲደርሱ ያስተዋልን ሲሆን ፍፁም ጥላሁን ያሻገረለት ኳስ ብሩክ ዓለማየሁ መሬት ለመሬት መትቶ ግብ ጠባቂው ያገደበት አስቆጪው ሙከራ እንዲሁም የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ እራሱ ብሩክ ዓለማየሁ ከሳጥን ውጪ መትቶ ለግብ ጠባቂው ጠንካራ ሳይሆን የቀረው ሌላኛው ሙከራ ሲጠቀስ አንፃራዊ የምድረገነት ሽረን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ያስመለከተን አጋማሹ ተገባዶ ግብ ሳይቆጠርበት ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ጨዋታው ሲመለስ ሁለቱም ቡድኖች ቀዳሚ የሚያደርጋቸው ግብ ለማግኘት የተጋጣሚዎቻቸውን ግብ ክልል እየደረሱ ተከላካይ መስመሮቻቸውን መፈተን የቻሉ ቢሆንም በሚቆራረጡ ኳሶች አደገኛ ሙከራዎችን ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ሆኖም ግን አስቆጪ የሚባሉ አጋጣሚዎችን በማድረግ ረገድ ፈረሰኞቹ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ከሳጥን ውጪ ሆነው በሚያደርጉት ሙከራ ግብ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል።

ጨዋታው 75ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የሽረው የተከላካይ መስመር ተጫዋች ፀጋአብ ዩሐንስ ጥፋት ሰርቶ ቢጫ ካርድ ሳይመለከት ቶሎ ተቀይሮ ሜዳውን ለቆ በመውጣት መልበሻ ክፍል ሲሮጥ የእለቱ ዋና ዳኛ በሁለት ቢጫ ካርድ በቀይ ከሜዳ ያሰናበቱበት አወዛጋቢው ክስተት ሲጠቀስ የጎዶሎ ተጫዋች ክፍተቱን ለመጠቀም ፈረሰኞቹ ወደፊት እየገቡ ጫና መፍጠር የቻሉ ቢሆንም የጠራ ሙከራ በአንድ አጋጣሚ ብቻ አድርገው ግብ ጠባቂው አግዶባቸው ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ደርሶ ጭማሪ ስድስት ደቂቃ በታየው ላይ የሜዳ መብራት በመጥፋቱ ጨዋታው ለመቋረጠ ተገዶ የነበረ ሲሆን አወዳዳሪው አካል ጨዋታውን አራዝሞ በራዘው እለት ቀሪዎቹ ስድስት ደቂቃዎች ተደርገዋል።

እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ሶስት ነጥብ ለማግኘት ሽረዎች በሙሉ ኃይላቸው እያጠቁ በሁለት አጋጣሚዎች አደገኛ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ጨዋታው ግብ ሳይቆጠርበት ተቋጭቷል።