ባህር ዳር ከተማዎች ከከፍተኛ ሊጉ ሁለት አዳዲስ ፈራሚዎችን ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

ዝውውራቸውን በይፋ የቀጠሉት ባህር ዳር ከተማዎች ስብስባቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ከከፍተኛ ሊጉ ሁለት ተስፋ ሰጪ ተጫዋቾችን ማስፈረማቸውን አረጋግጠዋል። የመጀመሪያው አዲስ ፈራሚ ቀደም ሲል በወሊሶ፣ ዳሞት ከተማ እና እንዲሁም ባለፈው የውድድር ዓመት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ስኬታማ ቆይታ ያደረገው ግብ ጠባቂው ሃይደር ሙደሲር ሲሆን በ2017 የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ ድንቅ ብቃቱን በማሳየት የዓመቱ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ መመረጡ የሚታወስ ነው።
ሌላኛው ውሃ ሰማያዊውን ማሊያ ለመልበስ የተስማማው ደግሞ ወጣቱ መስመር አጥቂው ማስተዋል ጋቻፎ ነው። የእግር ኳስ ጅማሮውን ከወላይታ ዲቻ ከ20 ዓመት በታች ቡድን በመጀመር የተነሳው ይህ ወጣት አጥቂ ባለፈው የውድድር ዘመን በቦዲቲ ከተማ ማሊያ ያሳየው አስደናቂ እና ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ የአሰልጣኝ ደግአረገን ቀልብ መሳብ ችሏል። አሁን ደግሞ በይፋ የጣና ሞገዶቹን ውሃ ሰማያዊ ማሊያ በመልበስ ለአዲሱ የውድድር ዘመን የምንመለከተው ይሆናል።

