የግብ ዘቡ ረቡዕ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናል

የግብ ዘቡ ረቡዕ ወደ ደቡብ አፍሪካ ያቀናል

ሶከር ኢትዮጵያ በቀዳሚነት ባጋራችው መረጃ መሠረት የብሔራዊ ቡድኑ ቁጥር አንድ ተመራጭ ግብ ጠባቂ የፊታችን ረቡዕ ወደ ደቡብ አፍሪካ ይጓዛል።

የእግርኳስ ሕይወቱን በኢሊባቡር ከተማ ሱፔ በተባለች ገጠራማ መንደር ጀምሮ ለወሎ ኮምቦልቻ፣ ለጅማ ከተማ ፣ ለባህር ዳር ከተማ በመጫወት አሳልፎ ከኢትዮጵያ መድን ጋር የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ስኬታማ ዓመታትን እያሳለፈ የሚገኘው ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ወደ ደቡብ አፍሪካው ክለብ ለሙከራ እንደሚያቀና ሶከር ኢትዮጵያ አስቀድማ ገልጻ ነበር።

አሁን አቡበከር ኑራ እንደነገረን ከሆነ የፊታችን ረቡዕ ሰኔ 17 ቀን በማለዳው በረራ ወደ ደቡብ አፍሪካ እንደሚጓዝ ገልፆ ምንም እንኳን የሙከራ ዕድሉን ያመቻቸለት ክለብ ማን እንደሆነ ለጊዜው መግለፅ ባይፈልግም በቅርብ ዓመታት በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፊ የነበረ ክለብ መሆኑን ጠቁሞናል።

የግብ ዘቡ ወደ ስፍራው ካቀና በኋላ የሙከራውን ሂደቱን በተመለከተ የሚኖረውን መረጃ እንደሚያደርሰን ገልፆልናል። አቡበከር በሦስት ዓመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ የሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂነት ክብር መቀዳጀቱ ይታወሳል።