መረጃዎች | 32ኛ የጨዋታ ቀን

9ኛው የጨዋታ ሳምንት የሚጀምርባቸውን የነገ ሁለት ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

መቻል ከ ሲዳማ ቡና

እንደተጠበቁት ሳይሆኑ አሁን ላይ ከሰንጠረዡ አጋማሽ በታች የሚገኙት መቻል እና ሲዳማ የነገ ቀዳሚ ተጋጣሚዎች ናቸው። ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ከድል ጋር ያልተገናኘው መቻል አሁንም የምርጥ ስብስቡን አቅም ለማግኘት እየተቸገረ ይገኛል። በአዲሱ አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ ስር በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ረገድ መሻሻል እያሳየ የነበረው ሲዳማ ቡናም በ7ኛ ሳምንት በሊጉ መሪ ኢትዮጵያ መድን አስደንጋጭ የ4-0 ሽንፈት አስተናግዶ ለዚህ ጨዋታ ደርሷል።

ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር መረቡን ሳያስደፍር የወጣው መቻል ከጨዋታው የሚወስደው ጠንካራ ጎን ይኸው የመከላከል መዋቅሩ ነው። በእርግጥ በአመዛኙ በራሳቸው ሜዳ ላይ ያሳለፉት የመስመር ተከላካዮቹ ቁጥብነት ቡድኑን ከፊት የሜዳውን ስፋት በመጠቀም የማጥቃቱን አድማስ እንዳያሰፋ ያደረገው ይመስላል። መቻሎች በማጥቃቱ ረገድ ከወገብ በላይ ባለው ቡድናቸው ላይ ፍፁም ዓለሙ እና ከነዓን ማርክነህን አፈራርቀው በመጠቀም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚጠቀሙበትን መንገድ ለመቀየር እየሞከሩ ይገኛሉ። ከዚህ የአማካይ ክፍል ቀመር ባለፈ በጊዮርጊሱ ጨዋታ በረከት ደስታንም በተጠባባቂነት ማስጀመራቸው በመስመር ጥቃታቸውም ላይ ለውጦችን በማድረግ ትክክለኛው ቅርፅ ላይ ለመድረስ መንገድ ላይ ስለመሆናቸው ማሳያ ነው። ነገም የመቻል ትልቁ ፈተና ከወገብ በላይ ያለው የቡድኑ ክፍል በአጠቃላይ የጨዋታ አቀራረቡ ታግዞ በቂ ዕድሎችን አለፍ ሲልም ግቦችን ያሳየናል ወይ የሚለው ነጥብ ይሆናል።

ሲዳማ ቡና በኢትዮጵያ መድን በተረታበት ጨዋታ በአጠቃላይ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ መጥፎ ባይሆንም የኋላ መስመሩ ውቅር ክፍተት ገና በጊዜ እጅ እንዲሰጥ አድርጎታል። የመሐል ተከላካዮቹ ጊት እና ያኩቡም ከኳስ ጋር እና ከኳስ ውጪ የነበራቸው አቋም እጅግ ወርዶ ፈጣኖቹን የመድን አጥቂዎች መቋቋም ሳይችሉ ቀርተዋል። የአማካይ መስመሩም ከኳስ ውጪ እጅግ ታታሪ በነበረው የመድን ክፍል ብልጫ ተወስዶበት ነበር። ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች የተሸነፈው ሲዳማ ቶሎ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይህንን ክፍተት አሻሽሎ አብዝቶ የሚጠቀመውን የመስመር አጨዋወት ማጠናከር የግድ ይለዋል። የቡድኑ የልብ ምት የሆነው ፍሬውም ዋነኛ ኃላፊነቱን እንዲወጣ የማጥቃት ነፃነት መመለስ የሚያስፈልግ ይመስላል።

አምና በሁለተኛው ዙር ሲገናኙ ስምንት ግቦችን ያሳዩን ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን በ22 ጨዋታዎች የተገናኙት ሲሆን 45 ጎሎችን አስቆጥረዋል። ዕኩል ሰባት ጊዜ ተሸናንፈው ስምንት ጊዜ አቻ ሲለያዩ መቻል 23 ሲዳማ ደግሞ 22 ግቦችን አስመዝግበዋል።

ነገ ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው ፊሽካ የሚጀመር ሲሆን መቻል ተሾመ በላቸውን እንዲሁም ሲዳማ ቡና ሳላዲን ሰዒድን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። ከዚህ በተጨማሪ ሲዳማ ቡና መክብብ ደገፉን በቅጣት ሲያጣ ቅጣት ላይ የነበረው ሌላኛው ግብ ጠባቂ ፍሊፕ ኦቬኖ ደግሞ ከቅጣት ይመለስለታል።

ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ምሽት ላይ የሚደረገው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ 2ኛ ደረጃን እያሰበ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ወደ አንደኝነቱ ለመመለስ የሚያደርጉት እንደመሆኑ ከፍ ያለ ግምት ይሰጠዋል። ሽንፈት ካስተናገደ አምስት የጨዋታ ሳምንታት ያሳለፈው ሀዋሳ ከተማ ፋሲል እና ሲዳማን ረትቶ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በመጨረሻ ደቂቃ ጎሎች ነጥብ ተጋርቶ ለነገው ጨዋታ ደርሷል። በተከታታይ አራት ድሎች ሊጉን የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ ከአንድ ሽንፈት እና ከሦስት ተከታታይ አቻዎች በኋላ ሙሉ ሦስት ነጥብ ወደ ማስካት ለመመለስ የነገውን ጨዋታ ይጠብቃሉ።

በሊጉ አስደናቂ አጀማመር ማድረግ ችሎ የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጠንካራ ጉዞው ለዘብ ማለቱ ከነገው ጨዋታ የሚገኘውን ውጤት አጥብቆ እንዲፈልገው ያደርገዋል። ተደጋጋሚ ድል ከማሳካት የሚመነጨውን እና ከጨዋታ አስቀድሞ ተጋጣሚ ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥረውን የሥነ ልቦና ብርታት ለመመለስም በቶሎ ወደ ማሸነፉ መምጣት ለቅዱስ ጊዮርጊስ የግድ ይመስላል። ከዳዊት ተፈራ ጉዳት በኋላ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ ኃላፊነቱን ለቢኒያም በላይ የሰጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመስመር ሲነሳ ይበልጥ ተፅዕኖው የሚጎላው ቢኒያምን ሙሉ አቅም ያገኘ አይመስልም። በመጀመሪያ ደቂቃዎች ተደጋጋሚ ጫናዎችን በመፍጠር ጨዋታን በቶሎ መግደል እና ከተለያዩ ተሰላፊዎቹ ግቦችን የማግኘት የቅርብ ጊዜ የፈረሰኞቹ ባህሪን መልሶ ማግኘት የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ዋነኛው የቤት ሥራ ይሆናል። በዚህ ውስጥ በጥልቀት ተከላክሎ በፈጣን ጥቃት መውጣት ከሚያውቅበት ሀዋሳ ከተማ ጋር በተለይም በተጋጣሚ ሜዳ ላይ የሚገጥመው ፈተና ቀላል እንደማይሆን መገመት ይቻላል።

ሀዋሳ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና በመጨረሻ ውጤት የወሰደበት መንገድ ከነገው ትልቅ ፍልሚያ በፊት ሊኖረው የሚገባው ጥሩ የመጨረሻ ትውስታ ነው ማለት ይቻላል። ቡድኑ ጠንካራ የሚባለውን የማጥቃት ባህሪውን ባሳየበት ሁለተኛ አጋማሽ በዋናነት የመስመር ተጫዋቾቹን ፍጥነት በመጠቀም እና ሙጂብ ቃሲምን ያነጣጠሩ የአየር ላይ ኳሶች በማዘውተር ሲንቀሳቀስ ነበር። ። አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ይህንኑ ብቃት በነገው ጨዋታም እንደሚጠብቁ ዕሙን ነው። ከኳስ ውጪ በራሱ ሜዳ ላይ የሚቆይ ኳስ ሲያገኝ በኤፍሬም አሻሞ እና ዓሊ ሱለይማን ፍጥነት ተጠቅሞ ወደ ሙጂብ ከባድ ኳሶችን የሚያደርስ የሀይቆቹ ባህሪ ነገም ይጠበቃል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ በሆሳዕናው ጨዋታ እንዲቸገር ያደረገውን የአማካይ መስመር ድክመት በነገ ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተመሳሳይ ጫና ከደረሰበት በድጋሚ መልሶ ለማገገም ሊቸገር ይችላል።

ሁለቱ ቡድኖች ነገ ለ45ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። በእስካሁኖቹ ጨዋታዎቻቸው 77 ግቦችን ያስቆጠሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 27 ጊዜ ባለድል ሲሆኑ 34 ግቦች ያሏቸው ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ ሰባት ጊዜ አሸንፈዋል።

በኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ መሪነት በሚከናወነው ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በረከት ሳሙኤልን ከመጠነኛ ጉዳት እዮብ ዓለማየሁን ደግሞ ከአንድ ጨዋታ ቅጣት መልስ ሲያገኝ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ ዳዊት ተፈራ ፣ ሻይዱ ሙስጠፋ እና ተመስገን ዮሐንስ አሁንም ጉዳት ላይ ይገኛሉ።