የሜዳ ለውጥ ተደርጎበት በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የተከናወነው የጦና ንቦቹ እና የአዞዎቹ ጨዋታ በወላይታ ድቻ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ወላይታ ድቻ ነጥብ ተጋርቶ ከወጣው ከባለፈው አስተላለፍ አራት ተጫዋቾችን ለውጠዋል። በዚህም ፍፁም ግርማ፣ ቴውድሮስ ታፈሰ፣ መሳይ ሰለሞን እና ዘላለም አባተ በተስፋዬ መላኩ፣ ሙሉቀን አዲሱ፣ ካርሎስ ዳምጠው እና ያሬድ ደርዛ ተክተዋል። ከሽንፈት መልስ ለዚህ ጨዋታ የቀረቡት አርባምንጭ ከተማዎች ደግሞ ተመስገን ኢሳያስ፣ መሪሁን መስቀለ፣ እንዳልካቸው መስፍን እና ታምራት ኢያሱን በአካሉ አትሞ፣ ቡታቃ ሸመና፣ አሸናፊ ተገኝ እና ፍቃዱ መኮንን በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ፌደራል ዋና ዳኛ አባይነህ ሙላት ያስጀመሩት ይህ ጨዋታ ገና በ4ኛው ደቂቃ ነበር ቻርልስ ሪባኑ ከርቀት የመታውን ግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ ወደ ውጭ ባወጣው ጠንካራ ሙከራ ነበር ጨዋታው ከፍ ባለ ግለት መካሄድ የጀመረው። ሁለቱም ቡድኖች ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም እና ኳሶች ከተቃራኒ ሜዳ ተመስርቶ እንዳይወጣ በሚደረግ የማፈን ፍልሚያ ላይ ቀዳሚ ለመሆን በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ ወላይታ ድቻዎች በ18ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ጎል ያገኙት። ከግራ መስመር አርባምንጮች ከሜዳቸው ለመውጣት በሚያደርጉት ቅብብሎች መሐል የተፈጠረውን ስህተት ሙሉቀን አዲሱ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ በአስደናቂ ሁኔታ ኳሷን ከርቀት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ሜዳ ላይ ለመሸናነፍ የሚታየው እንቅስቃሴ በርከት ካሉ የደጋፊዎች ድባብ ጋር ታጅቦ የነበረው ፉክክር ጨዋታውን ሳቢ ቢያደርገውም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለመመልከት ብዙ ደቂቃ መቆየት አስፈልጎ ነበር። በዚህም አጋማሹ መውጫ 45ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ኳሱን እየገፋ የገባው ጸጋዬ ብርሃኑ ከሳጥን ውጭ ለቆመው ብዙአየሁ አቀብሎት አማካዩ በጥሩ ሁኔታ የመታውን ግብ ጠባቂው ኢድሪስ ጎል እንዳይሆን ከልክሎታል።
ብዙ ሳይቆይ ከዚህ ጥቃት በኋላ የጦና ንቦቹ የጎል መጠናቸውን ወደ ሁለት ከፍ ያሉበትን ጎል 45+3 ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። በተደጋጋሚ በቀኝ መስመር እግሩ ኳስ ሲገባ አደጋ ይፈጥር የነበረው ጸጋዬ ብርሃኑ አመቻችቶ ያቀበለውን ካርሎስ ዳምጠው በጥሩ እርጋታ ጎል አስቆጥሮ ደጋፊዎችን ወደ በለጠ ፈንጠዝያ አስገብቶ ጨዋታው ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ አሰልጣኝ በረከት ደሙ ቡታቃ ሸመና እና አሸናፊ ተገኝን አስወጥተው እንዳልካቸው መስፍን እና ታምራት ኢያሱን ቀይረው ያስገቡበት መንገድ ውጤታማ አድርጓቸው በጨዋታው የሚቆዩበትን ጎል በ47ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። እንዳልካቸው መስፍን ከማዕዘን ምት ያሻገረውን በተከላካዮች ሲመለስ የተደረበውን በርናድ ኦቼንግ ያቀበለውን አህመድ ሁሴን ጎል አድርጎታል።
የጨዋታው ግለት ሳይቀንስ አዞዎቹ ወደ ወደ ጨዋታው ቶሎ ለመመለስ ጥረት በማድረግ በአንፃሩ የጦና ንቦች ማጥቃቱን ሳይዘነጉ የጥንቃቄ አጨዋወት ምርጫቸው አድርገው በዘለቀው ጨዋታ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳንመለከት ቆይተናል። ጉሽሚያ በዝቶበት በቀጠለው የመጨረሻዎቹ የጨዋታው ደቂቃዎች አርባምንጭ ከተማዎች ያላቸውን አቅም በመጠቀም ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ጥረት ቢያደርጉም ወላይታ ድቻዎቸ በጥንቃቄ ውጤቱ ከእጃቸው እንዳይወጣ በማድረግ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀው ጨዋታውን 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፈው ወጥተዋል።