ሪፖርት | አዳማ ከተማዎች ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል

ሪፖርት | አዳማ ከተማዎች ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ከናፈቃቸው ድል ጋር ታርቀዋል

አዳማ ከተማ በስንታየሁ መንግሥቱ ብቸኛ ጎል ፈረሰኞቹን አሸንፎ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚደረገው ፉክክር አለሁ ብሏል።

በተከታታይ ድል እያደረጉ ለዚህኛው ሳምንት ጨዋታ የደረሱት ፈረሰኞቹ ከባለፈው ጨዋታ አስተላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ጳውሎስ ከንቲባ፣ ሀብታሙ ጉልላት  እና ዳግማዊ አርአያ በሻይዱ ሙስጠፋ አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ እና ቢኒያም ፍቅሩ ተክተው ሲገቡ ነጥብ ተጋርተው ለዚህ ጨዋታ የደረሱት አዳማዎች ባደረጉት የሁለት ተጫዋች ለውጥ ሙሴ ኪሮስ እና ነቢል ኑሪ አሳርፈው አሜ መሐመድ እና ቢንያም አይተን አስገብተዋል።

ፌደራል ዋና ዳኛ ሃይማኖት አዳና ባስጀመረው እና በማያድግ ኳስ እና በሚቆራረጥ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎችን ባስመለከተን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአመዛኙ መሐል ሜዳ ላይ በይበልጥ ትኩረትን ያደረጉ አጨዋወቶች የተበራከቱበት ነበር። አዳማዎች በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ወደ ፊት ተስበው በመሄድ በ17ኛው ደቂቃ ከአሜ መሐመድ የተላከለትን አድናን ረሻድ ጥሩ የጎል አጋጣሚ አግኝቶ ሳይጠቀምበት ከቀረው ለጎል ያልቀረበ ሙከራ ውጭ ሌላ የሚጠቀስ ዒላማውን የጠበቀ ዕድሎች ሳይፈጠር ወደ ውሃ ዕረፍት አምርተዋል።

በአንፃሩ ከውሃ ዕረፍት መልስ የተሻለ ወደ ፊት የመጠጋት ብልጫ ያየንባቸው ፈረሰኞቹ 27ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም ፍቅሩ ሳጥን ውስጥ ያቀበለውን አማኑኤል ኤርቦ በቀጥታ መቶት ምቱ ደካማ የነበረ በመሆኑ በቀላሉ ግብ ጠባቂው ዳግም የያዘው እንዲሁም ከደቂቃዎች በኋላ በተመሳሳይ በጥሩ እንቅስቃሴ ኳሱን ተቀባብለው አብዱልሃፊዝ ቶፊቅ በቀላሉ የመታው ኳስ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ብልጫ በወሰዱበት የመጨረሻዎቹ አርባ ደቂቃዎች የፈጠሩት ዕድሎች ነበሩ።

በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት የገቡት አዳማዎች በ45ኛው ደቂቃ ላይ ከቢንያም አይተን የተቀበለውን ስንታየሁ ቺፕ አድርጎ ለአድናን አቀብሎት እርሱም በደረቱ ያወረደለትን አጥቂው ስንታየሁ መንግስቱ በግሩም ሁኔታ ከሳጥን ውጭ መቶ ኳሷን መረቡ ላይ አሳርፎት አጋማሹ በአዳማዎች 1-0 በሆነ ውጤት አጋማሹ ተገባዷል።

ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ፈረሰኞቹ ወደ ጨዋታው በፍጥነት በመግባት ምላሽ ለመስጠት በተሻለ የኳስ ቁጥጥር መንቀሳቀስ ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በቀላሉ የሚያበላሿቸው ኳሶች የግብ ዕድልን በመፍጠሩ በኩል የተዋጣላቸው እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል። አዳማዎች ኳስ ሲያጡ ጥቃቶች እንዳይፈፀምባቸው በጠንካራ የመከላከል አደረጃጀታቸው ንቁ በመሆን ኳሶችን ሲያገኙ ደግሞ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር አደገኛው ቀጠና ቢደርሱም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ግን አልቻሉም።

ጨዋታው በዚህ ሂደት ቀጥሎ እያለ 77ኛው ደቂቃ ላይ አሳዛኝ የሜዳ ላይ ጉዳት ተከስቶ ጨዋታው ለመቋረጥ ተገዷል። ከስንታየሁ በኩል ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን አሜ መሐመድ ኳሱን ለማግኘት ግብጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ኳሱን ለማራቅ በሚያደርጉት ጥረት ተጋጭተው አሜ መሐመድ ከበድ ያለ ጉዳት አስተናግዶ ለተሻለ ህክምና በአንቡላንስ ሲሄድ ግብ ጠባቂው ባህሩ ህክምናውን ጨርሶ ወደ ጨዋታው ተመልሷል።

የተቋረጠው ጨዋታ ተመልሶ ባሉት ቀሪ ደቂቃዎች ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ በሁለት አጋጣሚዎች በተለይ በ90+7ኛው ደቂቃ ቢኒያም ፍቅሩ ጥሩ አጋጣሚ አግኝቶ ኳሱን ወደ ሰማይ የላካት የሚያስቆጭ አጋጣሚ ሆኖ ጨዋታው በአዳማ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።