በሰንጠረዡ በሁለት የተለያየ ፅንፍ በሃያ ነጥብ ልዩነት የተቀመጡት ቡድኖች ከድል ጋር ለመታረቅ የሚያደርጉት ጨዋታ የ29ኛው ሳምንት መገባደጃ መርሐግብር ነው።
በአርባ ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች 4ኛ ደረጃን ለመቆናጠጥ ስሑል ሽረን ይገጥማሉ።
ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አገግመው ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሦስት ድሎች እና ሁለት የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት መቻሎች በቅርብ ሳምንታት በውጤትም ሆነ በእንቅስቃሴ ረገድ መሻሻሎች አሳይተዋል፤ ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ መጋራቱ ጎዳው እንጂ ወደ መሪዎቹ የመጠጋት ዕድልም ነበረው። መቻሎች በተከታታይ ሁለት መርሐግብሮች ነጥብ መጋራት ቢችሉም በጨዋታዎቹ የነበራቸው ብቃት ግን ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። በተለይም ብርቱ ፉክክር፣ ሳቢ እንቅስቃሴ እና አራት ግቦች ባስመለከተን ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ የተለያዩበት ጨዋታ ያሳዩት ብቃት በርከት ያሉ አወንታዊ ጎኖች የታዩበት ነበር። ሆኖም የደረጃ መሻሻል ሊያስገኝላቸው በሚችለው የነገው ጨዋታ ከሁለት መርሐግብሮች በኋላ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ በአራት ጨዋታዎች ግብ ሳያስተናግድ ከዘለቀ በኃላ በመጨረሻው ሳምንት ሁለት ግቦች ባስተናገደው የኋላ ክፍል የታዩት ውስን የመከላከል ድክመቶች መቅረፍ ይኖርባቸዋል። በወጥነት መዝለቅ ያልቻለው የግብ ማስቆጠር አቅማቸውም ሌላው መስተካከል የሚገባው ነው።
በሃያ ነጥቦች 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ስሑል ሽረዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት በሚደረገው ፍልሚያ ወደ ኋላ ላለመቅረት ድልን እያለሙ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች በመደዳ ነጥብ ተጋርተው መውጣት የቻሉት ስሑል ሽረዎች አሁንም ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ከማገባደድ ችግራቸው መላቀቅ አልቻሉም። በሊጉ ከድሬዳዋ ከተማ በመቀጠል በርከት ያሉ የአቻ ውጤቶች ያስመዘገበው ቡድኑ ከተከታታይ ሽንፈቶች መላቀቁ እንደ አወንታ የሚነሳለት ነጥብ ቢሆንም ወልዋሎን ካሸነፈበት የ19ኛው ሳምንት ጨዋታ በኋላ ላለፉት ዘጠኝ መርሐግብሮች ከድል ጋር መራራቁ ደረጃው ከወራጅነት ፈቀቅ እንዳይል ከማድረጉም በላይ በቀጠናው ካሉ ሌሎች ክለቦች ያለውን ልዩነት አስፍቶታል። ቡድኑ ለከርሞ በሊጉ ለመሳተፍ የሚያደርገው ጉዞ ለማሳካትም ከድል ጋር መታረቅ ግድ ይለዋል፤ ይህ እንዲሆን ደግሞ በተለይም በቅርብ ሳምንታት የተስተዋሉበት የአጨራረስ ድክመቶች መቅረፍ እና አጠቃላይ የቡድኑን የማሸነፍ መንፈስ ከፍ የሚያደርጉ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል።
በመቻል በኩል ምንይሉ ወንድሙ እና አማኑኤል ዮሐንስ በጉዳት እንዲሁም አብዱልከሪም ወርቁ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆናቸው ታውቋል። በስሑል ሽረ በኩል ቅጣቱን ያልጨረሰው አምበሉ ነጻነት ገብረመድኅን እንዲሁም ክብሮም ብርሀነ እና አላዛር ሽመልስ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። ባለፈው ጨዋታ በጉዳት ምክንያት ያልተሳተፈው ኬቨን አርጉዲ ጨምሮ የተቀሩ የቡድኑ አባላት ግን ለጨዋታው ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ 3 ጊዜ ተገናኝተው
ሁለቱም በእኩሌታ አንድ አንድ ጨዋታዎች ላይ ድል ሲያደርጉ አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። በግንኙነቱ ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ 5 ግቦችን አስቆጥረዋል።