ሪፖርት | መቻል እና ስሑል ሽረ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | መቻል እና ስሑል ሽረ ነጥብ ተጋርተዋል

የጨዋታ ሳምንት መገባደጃ መርሐግብር መቻልን ከስሑል ሽረ አገናኝቶ 1ለ1 በሆነ ውጤት ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል።


መቻሎች በ28ኛው ሳምንት ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርተው ከወጡበት ቋሚ አሰላለፍ  የሶስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ፊልሞን ገ/ፃዲቅ፣ አማኑኤል ዩሐንስ እና በረከት ደስታን በማሳረፍ በምትካቸው ዩሐንስ መንግስቱ፣ ዮሴፍ ታረቀኝ እና ሽመልስ በቀለን ይዘው ሲቀርቡ ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው ከፋሲል ከተማ ጋር 1ለ1 ከተለያዩበት መጀመሪያ አሰላለፋቸው ክብሮም ብርሀነ እና አላዛር ሽመልስን በማሳረፍ ክፍሎም ገ/ሂወትን እና ሄኖክ ተወልደን ይዘው ገብተዋል።

በቀዛቃዛ አየር ጅማሮውን ያደረገው ጨዋታ በእንቅስቃሴ ረገድ ፈጣን ሽግግሮችን ቢያስመለክተንም በሙከራዎችን ግን መታጀብ አልቻለም።

ከደቂቃ ደቂቃ ጨዋታው ግለቱን እየጨመረ ቀጥሎ ጦሩ በተደጋጋሚ ወደ ተቃራኒ ቡድን ሜዳ ክፍል እየደረሰ ግብ መሆን የሚችሉ የተመቻቹ ኳሶችን ማግኘት ችለዋል፤ ሆኖም ግን አጨራረስ ላይ ሲቸገሩ አስተውለናል።

ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ወደ ሦስተኛው ሜዳ ክፍል በመድረሱ እንዲሁም ኳስ ፍሰት ተመጣጣኝ ፉክክር ማድረግ የቻሉ ቢሆንም የኋላ ኋላ የመቻሎችን ጫና ለመቋቋም በማሰብ ወደ ኋላ አፈግፍገው መልሶ ማጥቃትን የመጀመሪያ ምርጫቸውን ያደረጉበትን የመጀመሪያ አጋማሽ ከአካፋይ በኋላ ያሉትን ደቂቃዎች አሳለፈዋል።

ጦሩ በአጋማሹ አካፋይ በኋላ ሙሉ ትኩረታቸውን ሶስተኛው ሜዳ ክፍል ላይ በማድረግ መሪ ሊያደርጋቸው የሚችሉ አጋጣሚዎችን እየፈጠሩ ጫና ሲያሳድሩ ተመልክተናል። የመጀመሪያ አጋማሽ መገባደጃ ላይ ኮሊን ኮፊ ኩጆ በሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከቋሚ ርቆ ይለፍ እንጂ ጦሩን መሪ ለማድረግ ይበልጥ የቀረበ አደገኛ ሙከራ ነበር። አጋማሹም ከሙከራዎት ጋር ሳይታጀብ 0ለ0  በሆነ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታው ሲመለስ መቻሎች በአንፃራዊነት ጫን ብለው የስሑል ሽረዎችን ተከላካይ መስመር እየፈተኑ የግብ ማግባት ሙከራዎችን አድርገው የጥረታቸው ውጤት የሆነችዋን ግብ በ56ኛው ደቂቃ ላይ አግኝተዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ኮሊን ኮፊ በግራ መስመር ከኩል ያገኘውን ኳስ በስሑል ሽረ ተከላካዮች መካከል ያሳለፈለትን ኳስ ሸመልስ በቀል በጥሩ አጨራረስ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

የጨዋታ ብልጫ ተወስዶባቸው ግብ ያስተናገዱት ስሑል ሽረዎች የግቡ መቆጠር አነቃቅቷቸው የአቻነት ግብ ፍለጋ በርከት ብለው እየገቡ ሙከራዎትን አድርገዋል። በዚህም በ61ኛው ደቂቃ ላይ አብዲ ዋበላ በመስመር በኩል ኳስ እየገፋ ይዞ ገብቶ ወደ ግብ ሲያሻማ የመቻሎቹ ተከላካዮች ባደረጉት በእጅ ንኪኪ ምክንያት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ኤልያስ አህመድ ወደ ግብነት ቀይሮ አቻ አድርጓቸዋል።

ከአቻነት ግቧ በኋላ ጨዋታው ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ለተመልካች እያስመለከተ ቀጥሎ ሁለቱም ቡድኖች የማሸነፊያ ግብ ለማስቆጠር ወደፊት ቶሎ ቶሎ እየገቡ ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን ሙከራዎቹ ይሄን ያህል ከባድ የሚባሉ አልነበሩም። ሆኖም ግን በ75ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ከመሃል ሜዳ የተሰነጠቀውን ኳስ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አታሎ ለማለፍ ጥረት ሲያደርግ ሞይስ ፓዎቲ በጥሩ ቅልጥፍና ያገደበት አጋጣሚ የመቻሎች ወርቃማ እድል ቢሆንም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

በ81ኛው ደቂቃ ላይ ተጨራርፎ የተገኘውን ኳስ ኤልያስ አህመድ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከግቡ ርቆ ይለፍ እንጂ ስሑል ሽረዎችን ከመመራት ተነስተው መሪ እንዲሆኑ ለማስቻል ያቀረባቸው አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

ጦሩ በጨዋታ መገበዳጃ ላይ በይበልጥ ጫና ፈጥሮ ሙሉ ኃይላቸውን ቢጠቀሙም ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው ጨዋታው ነጥብ በማጋራት ተጠናቋል።