ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ መድን ከ ሲዳማ ቡና

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ኢትዮጵያ መድን ከ ሲዳማ ቡና

የ32ኛው ሳምንት የነጥብ ልዩነቱ ለማስቀጠል ወይም ለማስፋት የሚያልመው መሪው መድን እና በስምንት ውጤታማ ጨዋታዎች ከወራጅነት ስጋት ወደ ሊጉ አናት የተጠጋው ሲዳማ ቡና በሚያደርጉት እጅግ ተጠባቂ ጨዋታ ይጀመራል።

ስልሳ ነጥብ ሰብስበው ከተከታያቸው ኢትዮጵያ ቡና በስድስት ነጥቦች ልቀው ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች በመጨረሻው ሳምንት ከገጠማቸው ሽንፈት ለማገገም ሲዳማ ቡናን ይገጥማሉ።

ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኋላ እጅግ ከባድ ፍልሚያ በተደረገበት መርሐግብር በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ያስተናገዱት መድኖች በወሳኙ ጨዋታ ያሳዩት እንቅስቃሴ መልካም ቢሆንም የተጋጣሚያቸውን ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ግብ ማስቆጠር ባለመቻላቸው ሽንፈት ለማስተናገድ ተገደዋል። መድኖች ለዋንጫ የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያደላድሉበትን ዕድል ባይጠቀሙም ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ያደረጉት ተጋድሎ እንዲሁም በግቦች ባይታጀብም ያሳዩት ጥረት በአወንታነቱ የሚጠቀስላቸው ነው። ሆኖም የነገው ተጋጣሚያቸውም በተመሳሳይ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ፣ ባለፉት ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ በአምስቱ መረቡን አስከብሮ የወጣ እና በተጠቀሱት መርሐግብሮች ሽንፈት ያልቀመሰ እንደመሆኑ የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት ከፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ለዋንጫ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ ከቀሩት መርሐግብሮች አንጻር ሲታይ ነገ ከባድ ጨዋታ የሚጠብቃቸው መድኖች ከሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በተጨማሪ በአእምሮ ደረጃ በላቀ ሁኔታ መገኘት በሚጠይቀው መድረክ እንደመኖራቸው የቡድኑን መንፈስ ከፍ ማድረግ የሚችሉ ሥራዎች መሥራትም ይኖርባቸዋል።

በአርባ ስድስት ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሲዳማ ቡናዎች በያዙት የውጤታማነት መንገድ በመቀጠል ደረጃቸውን የሚያሻሽሉበት ዕድል ለማመቻቸት የሊጉን መሪ ይገጥማሉ።

ነገ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ በአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ለማድረግ ወደ ሜዳ የሚገቡት ሲዳማ ቡናዎች በመቀመጫ ከተማቸው ሀዋሳ ባሳለፏቸው ስምንት ውጤታማ ሳምንታት እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስን ባሸነፉበት የአዳማ ከተማ የመጀመርያ ጨዋታ ላይ ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ ከወራጅነት ስጋት ወደ ሰንጠረዡ አናት ተመንድገዋል። በከተማቸው እና በደጋፊያቸው ፊት ባደረጉት የመጀመርያ ጨዋታ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ካስተናገዱ በኋላ ቀጥለው በተካሄዱ ስምንት መርሐግብሮች ላይ እጅ ያልሰጡት ሲዳማ ቡናዎች በተጠቀሱት ጨዋታዎች ሽንፈት ካለማስተናገዳቸው በተጨማሪ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገባቸው የውድድር ዓመቱ ጉዟቸውን አቃንቶታል።

ቡድኑ በመጨረሻዎቹ ስምንት የጨዋታ ሳምንታት ማግኘት ከሚገባው ሀያ አራት ነጥብ ውስጥ ሀያውን ማሳካቱ እንዲሁም በተጠቀሱት ጨዋታዎቹ በአምስቱ መረቡን አለማስደፈሩ በጠንካራ ጎኑ የሚጠቀስለት ቢሆንም በግብ ማስቆጠሩ ረገድ ያለው ብቃት ግን ከዚህም በላይ መሻሻል የሚገባው ነው። በቅርብ ሳምንታት የቡድኑ ድክመቶች በመቅረፍ ረገድ ውጤታማ ስራዎች የሰሩት አሰልጣኝ አዲሴ ካሳ በነገው ጨምሮ በቀጣይ ጨዋታዎች ባለፉት ስምንት መርሐግብሮች ውስጥ በሁለት አጋጣሚዎች ብቻ በጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ያስቆጠረውን የማጥቃት አጨዋወታቸውን ማሻሻል ግድ ይላቸዋል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል መሐመድ አበራ በጉዳት ምክንያት የነገው ጨዋታ የሚያመልጠው ይሆናል። በሲዳማ ቡና በኩል ጊት ጋትኮች በቅጣት አጥቂው ማይክል ኪፕሩቪ ደግሞ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆኑ ሬድዋን ናስር ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ የጀመረ ቢሆንም የመጫወቱ ነገር የአሰልጣኙን እና የህክምና ቡድኑን ውሳኔ ይጠብቃል። የተቀሩት የቡድኑ ስብስብ ተሟልተው የሚቀርቡ ይሆናል።

ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በሊጉ 11 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 5 ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተለያይተው ኢትዮጵያ መድን ደግም 1 ጨዋታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ሲዳማ ቡና 9 ኢትዮጵያ መድን ደግሞ  8 ግቦች አስቆጥረዋል።