ሪፖርት | ስሑል ሽረ በፈረሰኞቹ በተረቱበት ጨዋታ ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርደዋል

ሪፖርት | ስሑል ሽረ በፈረሰኞቹ በተረቱበት ጨዋታ ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርደዋል

የፍፁም ጥላሁን ብቸኛ ግብ ለፈረሰኞቹ ከሦስት ተከታታይ ሽንፈት በኋላ ድል ሲታጎናፅፍ ስሑል ሽረን ከሊጉ የመሰናበቱን ነገር እውን አድርጋለች።

የ32ኛ ጨዋታ ሳምንት የሦስተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በሊጉ ለመቆየት የዛሬውን ጨዋታ የግድ አሸንፈው ቀጣይ ጨዋታዎችን የሚጠብቁትን ስሑል ሽረዎችን ላለፋት ሦስት ጨዋታ ሳምንታት ከሶስት ነጥብ  ጋር መገናኘት ከተሳናቸውን እና ተከታታይ ሶስት ጨዋታ ሽንፈት ካስተናገዱት ከፈረሰኞቹ ጋር አገናኝቷል።

ስሑል ሸረ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በምዓም አናብስቶች 2ለ1 ስረቱ ይዘው ከገቡት የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ አድርገው አላዛር ሽመልስን በክፍሎም ገብረሂወት ተክተው ሲገቡ ፈረሰኞቹ በበኩላቸው በ31ኛው ጨዋታ ሳምንት በሲዳማ ቡና 1ለ0 ሲሸነፉ ይዘው ከገቡት ቋሚ አሰላለፍ አማኑኤል ተርፋ፣ ሆኖክ ዩሐንስ እና አማኑኤል አረቦ አሳርፈው በምትካቸው ብሩክ ታረቀኝ፣ ዳግማዊ አርኣያ እና ሀብታሙ ጉልላት ይዘው ገብተዋል።

ጥንቃቄ በተሞላ አቀራረበ ጅማሮውን ያደረገው ጨዋታው በእንቅስቃሴ ረገድ መጥፎ የሚባል ባይሆንም እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራዎች አላስመለከተንም። ይሁን እንጂ ቡድኖቹ ኳስ ተቆጥጥረው ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል እየደረሱ አጋጣሚዎችን መፍጠር ቢችሉም አጨራረስ ላይ ፍፁም ደካማ እንቅስቃሴ አድርገው ኳሶቹ በቀላሉ እየተበላሸባቸው ወደ ግብ መቀየር ሲሳናቸው አስተውለናል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ ፊት ደርሰው እድሎችን በመፍጠር አኳያ በአንፃራዊነት ብልጫ በወሰደቡበት በመጀመሪያው ጨዋታ ክፍለጊዜ በርከት ያሉ ግብ መሆን የሚችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ችለዋል፤  ሆኖም ግን ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ሰንብተዋል። ካደርጓቸው ሙከራዎች መካከል 20ኛው ደቂቃ ላይ መሃል ሜዳ አከባቢ ተጨራርፎ የተገኘውን ኳስ ቢንያም ፍቅሩ ግብ ጠባቂው መውጣቱን ተመልክቶ በረጅሙ የመታው ኳስ ከግቡ አግዳሚ ከፍ ብሎ ያለፈው እና በ33ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን በመስመር በኩል ኳስ እየገፋ ይዞ ገብቶ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ለነበረው የአብስራ ጎሳዬ አሻግሮለት ቀጥታ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ በአጋማሹ ሌላኛው በፈረሰኞቹ በኩል ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።

በዛሬው እለት ከሊጉ መውረዳቸውን ላለማረጋገጥ ግዴታ አሸናፊው መውጣት የሚጠበቅባቸው ስሑል ሽረዎች በበኩላቸው የአጋማሹ አካፋይ ድረስ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት እየሄዱ እድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ያስተዋልን ቢሆንም የኋላ ኋላ እንደመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መሆን አቅቷቸው እየተቀዛቀዙ ከፈረሰኞቹ የሚደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም ሲረባረቡ ከመመለከቱ ውጪ ወደ ፊት የመሄዱን ነገር ቀንሰው ሲንቀሳቀሱ አስተውለናል። አጋማሹም ግብ ሳይቆጠርበት ዐለ0 ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደጀመረ ኳስ ጀምረው ወደፊት ፈጣን ኳስ ይዘው የገቡት ፈረሰኞቹ ጥሩ የጎል ማግባት እድል አግንተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል፤ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ፋአድ አብደላ ሳጥን ውስጥ ብቻውን ለነበረው ቢኒያም ፍቅሩ አቃብሎት ከግብ ጠባቂው ጋር ፊት ለፍት ተገናኝተው ያመከነው አስቆጪው አጋጣሚ ይጠቀሳል።

ከአንደኛው አጋማሽ አንፃር በፈጣን ሽግግሮች የታጀበው ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች መካከል ጥሩ ፉክክር የታቸበትና በመልሶ ማጥቃት ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል እየደረሱ አጋጣሚዎችን የፈጠሩበት ነበር። በዚህም ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ፈረሰኞቹ ፍፁም በላይነትን ወስደው ጨዋታው ስልሳዎቹ ደቂቃዎች ዘልቋል።

በ65ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን ከሳጥን ውጪ ሆኖ አክርሮ ሲመታት ሞይስ ፓዎቲ እንዴትም ጨርፎ በማውጣት የማዕዘን ምት ሲያደርግ እራሱ ኳስ ተሻምቶ ከብዙ ጥረት በኋላ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። 66ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ጉልላት ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ ስሑል ሽረዎች አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት የተወሰነ ያህል ጫና ቢያደርጉም የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ ተስፋ የቆረጡ በሚመስል መልኩ በቅብብል ለመሄድ ጥረት ያደርጉ እንጂ አደገኛ ሙከራ ለማድረግ ሲጥሩ መመለከት አልቻልንም። ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር የግብ እድሎችን በተደጋጋሚ ሲፈጥሩ አስተውለናል። ምንም እንኳን ወደፊት ቢሄዱሙ ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ አምስት ደቂቃዎች አምርቷል። በ86ኛው ደቂቃ ላይ በቆመ ኳስ ፈረሰኞቹ ያደረጉት ሙከራ ሲታወስ ቢኒያም ፍቅሩ እና በረከት ወልዴ እዛው ተቀባብለው በረከት ወልዴ ጠንከራ ያለ ኳስ ወደ ግብ መጥቶ ግብ ጠባቂው በቀላሉ የተቆጣጠረባቸው ሙከራ ይተወሳል።

በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ስሑል ሽረዎች ለከረመው ውድድር አመት በሊጉ የመቆየት ጉዳይ በዛሬው ጨዋታ ላለማመረጋገጥ ቢያንስ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም ሙሉ ሶስት ነጥብ ለማግኘች ያለፉትን 270 ደቂቃዎች መጠበቅ ግድ የሆነባቸው ፈረሰኞቹ ነጥቡን አሳልፈው ላለመስጠት በጥንቃቄ ተጫውተው ጨዋታውን አገባደዋል። በዚህም የእለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በፍፁም ጥላሁን ብቻ ግብ ለፈረሰኞቹ ሶስት ነጥብ በማጎናፀፍ ፤ ስሑል ሽረዎችን ደግሞ ከሊጉ መውረዳቸውን በማረጋገጥ ጨዋታው ተቋጭቷል።