ብርቱካናማዎቹ ከስጋት ቀጠናው ጨርሶ ለመራቅ ከቢጫዎቹ ጋር የሚፋለሙበት ጨዋታ ቀትር ላይ ይከናወናል።
በውድድር ዓመቱ ለመጀመርያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ነጥባቸውን ሰላሣ ዘጠኝ
በማድረስ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች የተያያዙት የድል መንገድ ማስቀጠል ከወራጅ ቀጠናው ይበልጥ እንዲርቁ ይረዳቸዋል።
ብርቱካናማዎቹ ፋሲል ከነማን ካሸነፉበት ጨዋታ በኋላ በተከናወኑ አራት መርሐ-ግብሮች ላይ ተከታታይ ሦስት ሽንፈቶች እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ለወራጅነት ስጋቱ እጅግ መጠጋት ችለው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች በመደዳ ድል ማድረጋቸውን ተከትሎ ከወራጅ ቀጠናው በአምስት ነጥቦች ርቀት እንዲቀመጡ አስችሏቸዋል። በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ሙሉ ሦስት ነጥብ ሰብስበው በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙት ድሬዎች በቅርብ ሳምንታት በቡድናቸው ላይ በርከት ያሉ ለውጦች ተስተውለዋል፤ ከነዚህም በወሳኝ ወቅት ላይ በቡድኑ የተስተዋለው የድል ረሀብ እና የላቀ የማሸነፍ መንፈስ እንዲሁም የማጥቃት አጨዋወቱ መሻሻል ይጠቀሳሉ። በተለይም በአራት ጨዋታዎች ላይ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ኳስ እና መረብ ካገናኘ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወቱ በቡድኑ ውጤት ማማር የአምበሳውን ድርሻ ተወጥቷል።
በነገው ዕለት ግን በጠጣር አቀራረብ ኢትዮጵያ ቡናን ነጥብ አስጥሎ ወደ ጨዋታው የሚቀርበው ወልዋሎን እንደመግጠማቸው ምናልባትም ቡድኑ ወደ መከላከሉ ባዘነበለ አጨዋወት ሊቀርብ የሚችልበት ዕድል ስላለ የግብ ማግኛ አማራጮቻቸውን ማስፋት ይኖርባቸዋል።
በአስራ ስድስት ነጥቦች ግርጌው ላይ የተቀመጡት እና በውድድር ዓመቱ ምንም ዓይነት የደረጃ ለውጥ ባለማድረግ የሊጉ ብቸኛ ክለብ የሆኑት ወልዋሎዎች
ከሊጉ ቀድመው መውረዳቸውን ተከትሎ የቀጣይ መርሐ-ግብሮች ዋና ዓላማቸው ለክብር መጫወት ነው።
በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ በአንድ አጋጣሚ ብቻ ሽንፈት ያስተናገዱት ወልዋሎዎች በቅርብ ሳምንታት በውድድር ዓመቱ ከነበራቸው ብቃት አንፃር በብዙ ረገድ ተሻሽለዋል። በሊጉ ከአዳማ ከተማ ጋር በጣምራ በርከት ያሉ ግቦች በማስተናገድ ቀዳሚ የሆነው ቡድኑ ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ እንዲሁም ጠንካራው ኢትዮጵያ ቡና በገጠመበት የመጨረሻ ጨዋታ ላይ ያሳየው የመከላከል ብርታትም የኋላ ክፍሉ እንደተሻሻለ ማሳያዎች ናቸው። በነገው ዕለትም በተመሳሳይ ጠንካራ እና ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦች ያስቆጠረ እንዲሁም ከውጤት ፈላጊነት አንፃር ከፍ ባለ የማጥቃት አጨዋወት ይቀርባል ተብሎ የሚጠበቀው ቡድን እንደመግጠማቸው በመከላከሉ ረገድ በበቂ መጠን መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪም በመጨረሻው ጨዋታ በቂ የግብ ዕድሎች ያልፈጠረው የማጥቃት አጨዋወት ማሻሻል ከአሰልጣኝ አታክልቲ በርኸ ቡድን የሚጠበቅ ነው።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል መሐመድኑር ናስር በጉዳት፤ አሕመድ ረሺድ እና አቤል አሰበ ደግሞ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው። በወልዋሎ በኩል ጉዳት ላይ የነበሩት ቡልቻ ሹራ፣ ዳዋ ሆቴሳ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ሳምሶን ጥላሁን ከጉዳታቸው ስያገግሙ ተከላካዩ ሳምሶን ተካ ግን በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን ባደረጓቸው 5 ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከተማ ሦስቱን በማሸነፍ የበላይ ሲሆን በ2 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተው ወልዋሎ እስካሁን ድል ማሳካት አልቻለም። በአራቱ ግንኙነቶች ድሬዳዋ 7፣ ወልዋሎ 2 ጎል አስቆጥረዋል።