ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ፋሲል ከነማ ከ አዳማ ከተማ

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ፋሲል ከነማ ከ አዳማ ከተማ

ነገ በተመሳሳይ ሰዓት ከሚደረጉ ሦስት መርሐግብሮች ውስጥ ከወራጅ ቀጠናው የመውጣት ፉክክር ላይ ተመሳሳይ ጉዳይ ያላቸው ተጋጣሚዎችን የሚያገናኘው ጨዋታ እጅግ ተጠባቂ ነው።

በአርባ አንድ ነጥቦች 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ፋሲል ከነማ ከሳምንታት ጥበቃ በኋላ ያገኘውን እጅግ ወሳኝ ድል በማስቀጠል ነጥቡን አርባ አራት  በመክተት ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ለመላቀቅ እንደሚጥር ይታሰባል።

ከተከታታይ ነጥብ መጣል በኋላ ወደ ድል መንገድ ቢመለስም ከዚያ በፊት በዘጠኝ ተከታታይ መርሐ-ግብሮች ነጥብ የጣለው ፋሲል ከነማ ከ 25ኛው እስከ 33ኛው ሳምንት በተከናወኑ ጨዋታዎች በጣላቸው ነጥቦች አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። ቡድኑ ከቅርብ ተፎካካሪው ጋር ባደረገው የመጨረሻው መርሐ-ግብር ድል አድርጎ ከሌሎች በቀጠናው የሚገኙ ቡድኖች አንፃር የተሻለ የመትረፍ ዕድል ቢኖረውም ከወራጅ ቀጠናው ያለውን የሦስት ነጥብ ርቀት በዚህ ጨዋታ ማስፋት ካልቻለም በመጨረሻው ሳምንት ጫና ውስጥ ሊገባ ይችላል። ስለዚህ የያዘውን የተሻለ የመትረፍ ዕድል ይበልጥ ለማለምለም በነገው ዕለት ማሸነፍ ግድ ይለዋል።

ይህ እንዲሆን ደግሞ በነገው ጨዋታ  በዋናነት የመከላከል አደረጃጀቱን ስለሚያጠናክርበት እና ግቦችን ስለሚያስቆጥርበት መንገድ አጥብቆ ማሰብ የሚገባው ይመስላል። ቡድኑ በአምስት መርሐ-ግብሮች ስምንት ግቦች ካስተናገደ በኋላ በመጨረሻው ጨዋታ መረቡን አስከብሮ መውጣት ቢችልም ተጋጣሚው አዳማ ከተማ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ከመረብ ጋር ያዋሀደ ጠንካራ የማጥቃት አጨዋወት ያለው ቡድን በመሆኑ የመከላከል አደረጃጀቱን ማሻሻል የቡድኑ አንገብጋቢ ስራ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ተጋጣሚው በተጠቀሱት አራት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን አስከብሮ የወጣ እንደመሆኑ ዐፄዎቹ ከጨዋታው ሙሉ ነጥብ ይዘው ለመውጣት የማጥቃት አጨዋወታቸውን ጥራት ከፍ ማድረግ ይኖርባቸዋል።

በተከታታይ አራት ጨዋታዎች ድል አድርጎ የመትረፍ ዕድሉን ያለመለመው አዳማ ከተማ ነጥቡን ሰላሳ ስምንት በማድረስ 16ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣል። በነገው ዕለት ድል ማድረግም በሊጉ የመቆየት ተስፋውን በራሱ ዕድል የሚወስንበት ዕድል ሊሰጠው ስለሚችል ውጤቱን እጅግ አጥብቆ ይፈልገዋል።

በ30ኛው ሳምንት ላይ በኢትዮጵያ ቡና ከገጠመው የሁለት ለባዶ ሽንፈት ውጭ ባለፉት ስድስት መርሐ-ግብሮች እጅ ያልሰጠው አዳማ ከተማ በቅርብ ሳምንታት ባስመዘገባቸው አስደናቂ ውጤቶች ከነበረበት አዘቅት ወጥቷል። ቡድኑ አሁንም ለ20 የጨዋታ ሳምንታት ከቆየበት የወራጅ ቀጠናው መውጣት ባይችልም ቢያንስ የመትረፍ ተስፋውን አለምልሞ የነገውን ጨዋታ እየተጠባበቀ ይገኛል። ከነገው ፍልሚያ ሙሉ ነጥብ ይዞ መውጣት ከቻለም ዕድሉ የሚያሰፋበት አጋጣሚ ስለሚያገኝ መርሐ-ግብሩ እጅግ ወሳኝ ነው።

የአሰልጣኝ አብዲ ቡሊ የነገ ቀዳሚ ዓላማ የቡድኑን ሁለንተናዊ ብቃት የማስቀጠል ጉዳይ ነው። ባለፉት አራት ጨዋታዎች ላይ የተዋጣለት አፈፃፀም የነበረው እና ዘጠኝ ግቦች ያስቆጠረው የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት እንዲሁም በተጠቀሱት አራት መርሐ-ግብሮች ላይ በአንድ ጨዋታ ብቻ መረቡን ያስደፈረው የመከላከል አደረጃጀትም በያዙት ውጤታማ መንገድ መቀጠል የሚገባቸው ሲሆን የቡድኑ ወጣት ተጫዋቾች ለውድድር ዓመቱ እጅግ ወሳኝ ጨዋታ በአእምሮ ረገድ ማዘጋጀትም ሌላው አሰልጣኙን የሚጠብቃቸው ስራ ነው።

አዳማ ከተማዎች መጥፎውን የውድድር ዓመት ሊያስረሳ የሚችል ድል አግኝተው በሊጉ ለመትረፍ የሚያደርጉት ጉዞ ለማሳለጥ ዐፄዎቹ ደግሞ ከሳምንታት ጥበቃ በኃላ ያገኙትን የወሳኝ ምዕራፍ ውድ ድል በማስቀጠል በሊጉ ለመቆየት የሚያደርጉት እጅግ ተጠባቂ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ይደረግባቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ መርሐ-ግብሮች አንዱ ነው።

ቡድኖቹ በሊጉ 16 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ በግንኙነታቸውም ያለፉትን ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ጨምሮ 9 ጊዜ አቻ ሲለያዩ 5 ጊዜ ፋሲል 2 ጊዜ ደግሞ አዳማ አሸንፏል። ዐፄዎቹ 17 ግቦችን ሲያስቆጥሩ አዳማዎች ደግሞ 10 አግብተዋል።