የጦና ንቦቹ ብርቱካናማዎቹን ተቀይሮ በገባው ቴዎድሮስ ሀይለማርያም ብቸኛ ጎል 1ለ0 በመርታት የዓመቱ አስራ ሦስተኛ ድላቸውን ሲያስመዘግቡ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው አስራ አንደኛውን ሽንፈት አስተናግደው ዓመቱን ፈፅመዋል።
ወላይታ ድቻ ከንግድ ባንኩ ሽንፈት የሦስት ድሬዳዋ ከተማዎች በሊጉ መቆየታቸውን ስሑል ሽረን በመርታት ካስመዘገቡበት ውጤት የስምንት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ነጥባቸውን ከፍ ለማድረግ በሊጉ የመጨረሻ ሳምንት ያደረጉት ጨዋታ ፈጣን አጀማመሮችን በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ያስተዋልንበት ቢመስልም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ግን ህይወት አልባ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የበዙበት ነበር። ወላይታ ድቻዎች ሁለቱን መስመሮች በጥልቀት በመጠቀም በተሻለ ለመንቀሳቀስ ሙከራ ያልተለያቸው ቢሆንም ጠንቃቃ የነበረውን የድሬዳዋ ከተማን የኋላ ክፍል ማስከፈቱ ከብዷቸው ተስተውሏል።
ከራሳቸው ሜዳ ከሚደረግ ቅብብል በኋላ የተጋጣሚያቸው ሜዳ ላይ ለመግባት ሲቸገሩ በተደጋጋሚ የታዩት ብርቱካናማዎቹ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች በተወሰነ መልኩ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት በጣሩበት አጋጣሚ በአጋማሹ የጭማሪ ደቂቃ 45+3 ላይ ከቅጣት ምት አቡበከር ወንድሙ በቀጥታ መቶ የግብ ዘቡ አብነት ይስሀቅ በቀላሉ የያዘበት አጋጣሚ ብቸኛዋ ዒላማ የጠበቀችዋ ሙከራ ሆና በጥቅሉ ደካማ የነበረው አጋማሽ ያለ ጎል ተጋምሷል
ካርሎስ ዳምጠውን በመሳይ ሠለሞን ዮናታን ኤልያስን በቴዎድሮስ ሀይለማርያም ተክተው ከዕረፍት የተመለሱት ድቻዎች በፈጣን መልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ከቆሙ ኳሶች በጊዜ አከታትለው አደገኛ ሙከራዎችን ሰንዝረዋል። 47ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ምት ምንተስኖት ተስፋዬ ሲያሻማ ውብሸት ክፍሌ ገጭቶ ያቀበለውን ኳስ ዐየር ላይ ያገኘው ቴዎድሮስ ሀይለማርያም በግንባር ገጭቶ ሔኖክ ሀሰን ከመስመር ላይ ያወጣት እና ከሦስት ደቂቃዎች መልስም በድጋሚ ከማዕዘን ምንተስኖት ያሻማትን ኳስ በጭንቅላት ተጨራርፋ የደረሰውን እዮብ ተስፋዬ በግንባር ገጭቶ የግቡን የቀኝ ቋሚ ብረትን ነክታ በኋላም ጀሚል ያዕቆብ ከራሱ ሜዳ ኳሷን ያራቀበት አጋጣሚ የጦና ንቦቹ ያደረጓቸው ተከታታይ ጥቃቶች ነበሩ።
የተጫዋች ለውጥን በማድረግ በአዲስ ጉልበት በሽግግር ለመንቀሳቀስ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች የሞከሩት ብርቱካናማዎቹ በ57ኛው ደቂቃ ቻርለስ ሙሴጌ ከቀኝ ወደ ጎል መቶ የግብ ዘቡ አብነት ይስሀቅ የተፋውን ሙህዲን ሙሳ እና ዮሐንስ ደረጀ አግኝተው ሲገባበዙ በመጨረሻም ዮሐንስ ቢመታም በአግዳሚ በኩል የሰደዳት እንዲሁም 66ኛው ደቂቃ ላይ ጀሚል ያዕቆብ ከቀኙ ሳጥን ጠርዝ አክርሮ መቶ አብነት በግሩም ብቃት ያወጣበት እጅግ ጠንካራዎች አጋጣሚዎች ናቸው። ግለታቸውን ከፍ በማድረግ በፈጣን መልሶ ማጥቃት የመጨረሻዎቹን አስራ አምስት ደቂቃዎች ብልጫውን የወሰዱት የጦና ንቦቹ 80ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል።
እዮብ ተስፋዬ ከመሐል ሜዳው ከተከላካይ ጀርባ የላካትን ኳስ ሔኖክ ሀሰን ለግብ ዘቡ አላዛር መርኔ ወደ ኋላ ገጭቶ ለማቀበል ሲል ያሳጠራትን ኳስ ከጀርባ ሆኖ ያገኘው ከዕረፍት መልስ ተቀይሮ በመግባት ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቴዎድሮስ ሀይለማርያም ከመረብ አሳርፎ ቡድኑ መሪ አድርጓል። በቀጣዮቹ የመጨረሻ ደቂቃዎች መሳይ ሠለሞን ለድቻ ሀቢብ ከማል ለድሬዳዋ ሙከራን አድርገው የነበረ ቢሆንም በመጨረሻም ጨዋታው ግን በወላይታ ድቻ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በክለቡ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ 48 ነጥቦችን በመያዝ የአመቱ አስራ ሦስተኛ ድልን ፣ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው አስራ አንደኛ ሽንፈታቸውን በማስተናገድ ዓመቱን ቋጭተዋል።