አርባምንጭ ከተማ በቡታቃ ሸመና ቅጣት ምት ጎል ሀዲያ ሆሳዕናን በመርታት ደረጃቸውን በማሻሻል ወድድር ዓመቱን ጨርሰዋል።
ሀዲያ ሆሳዕና በ35ኛው ጨዋታ ሳምንት በሻምፒዮኖቹ 3ለ2 ሽንፈት ባስተናገዱበት ጨዋታ ላይ ይዘው ከገቡት ቋሚ ስብስብ የስድስት ተጫዋች ለውጥ አድርገው ሲገቡ አርባምንጭ ከተማ በበኩላቸው በመጨረሻ ጨዋታ ከሲዳማ ቡና ጋር ያለ ግብ ሲለያዩ ይዘው ከገቡት ቋሚያቸው የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው ጨዋታውን ጀምረዋል።
የእለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ሁለት ለከርሞ በሊጉ መቆያቻውን አስቀደመው ቢያረጋግጡም ደረጃቸውን ለማሻሻል እና ነጥባቸውን ለማሳደግ ጥሩ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ የተጠበቁትን ሀዲያ ሆሳዕናን ከአርባምንጭ ከተማ አገናኝቷል። ሀዲያ ሆሳዕናዎች ገና ጨዋታው ጅማሮ ላይ ወደ ፊት ሄደው ፈጣን ግብ ለማስቆጠር የተቃረቡበትን ሙከራ አድርገው ጨዋታውን ሲጀምሩ አርባምንጭ ከተማዎች በአንፃራዊነት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሲያድርጉ ለመመለከት ሳንችል ቀርተናል።
ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ በቀጠለው በዚህ መርሐግብር ጨዋታው በእንቅስቃሴ አኳያ ደካማ የሚባል ባይሆንም ሀዲያ ሆሳዕና ሁለተኛው ደቂቃ ላይ የቆመ ኳስ ተሻምቶ አምበላቸው በረከት ወልደዩሐንስ ወደ ግብ መትቶ ለጥቂት ካለፈባቸው ሙከራ እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ 18ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማ ኳስ ተጨራርፎ በአሸናፊ ፊዳ አማካኝነት ወደ ግብነት ቢቀይሩም ከጨዋታ ውጪ ከተባለባቸው አጋጣሚ በስተቀር ቡድኖቹ ሶስተኛ ሜዳ ላይ ደርሰው ይሄ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ለግብ የቀረብ ሙከራ ሳያስመለክቱን ዘለግ ያሉ ደቂቃዎች ተቆጥረውበታል። በሚቆራርጡ ሽግግሮች ጋር ታጀቦ እምብዛም የግብ ማግባት ሙከራዎች ባላስመለከተን ጨዋታ አዞዎቹ የኋላ ኋላ ወደ ማጥቃት እንቅስቃሴ ገብተው ብልጫ መውሰድ ችለዋል።
ከረጅም ደቂቃዎች ጥበቃ በኋላ ጫን ብለው ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ እየገቡ ጫና ማሳደራቸውን የቀጠሉት አዞዎቹ ካደረጓቸው ሙከራዎቻቸው መካከል 32ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ተገኝ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በቀላሉ የተቆጣጠረበት እና 39ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ኳስ ይዞ ገብቶ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ለነበረው ቡጣቃ ሸመና ኳስ አሻግሮለት ወደ ግብ የመታውን ጠንካራ ያልነበረውን ኳስ ያሬድ በቀለ በቀላሉ የተቆጣጠረባቸው ሌላኛው ሙከራ ይጠቀሳል። ሀዲያ ሆሳዕናም የአጋማሹ መገባደጃ ላይ ከረጅም ደቂቃዎች በኋላ ጫላ ተሺታ በመስመር በኩል በረጅሙ የተጣለ ኳስ በፍጥነት ደርሶ ከኋላው ሲሮጥ ለነበረው ከማል ሀጂ አሻግሮለት ያደረገው የግብ ማግባት ሙከራ ብዙም ፈታኝ ሳይሆን ቀርቶ ግብ ጠባቂው ይቆጣጥር እንጂ ለግብ የቀረበ ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር።
ከእረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል አዞዎቹ አጋማሹ እንደጀመረ ፈጣን ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል፤ 49ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ላይ በተሰራ ጥፋት የተገኘውን የቆመ ኳስ ቡታቃ ሸመና ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ ሲመታ ኳሱ ኳሱን ለማገድ በቆሙ ተጫዋቾች ላይ ተጨርፎ ከመረብ ጋር ተገናኝቶ በግብ ቀዳሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሌላ ለግብ የቀረበ አጋጣሚ የፈጠሩት አዞዎቹ በአንድ ለአንድ ቅብብል ኳስ ይዘው ገብተው ግዙፉ አጥቂ አህመድ ሁሴን ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ መሪነታቸውን ለማጠናከር የቀረበ ኳስ ሳይጠቀም ቀርቷል። ሀዲያ ሆሳዕናዎችም የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ወደ ፊት እየሄዱ አጋጣሚዎች ሲፈጥሩ ብናስተውልም የጠራ መከራ ያደረጉት 56ኛው ደቂቃ ላይ ጫላ ተሺታ በአንድ ለአንድ ቅብብል የተገኘውን ኳስ ወደ ግብ መትቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ከቀረ በኋላ የአዞዎቹን ተከላካይ ከመፈተን በዘለለ ጠንካራ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ሰባዎቹ ደቂቃ ላይ ደርሷል።
ሀዲያዎች በቁጥር በርከት ብለው እየገቡ የአንድ ነጥብ ፍለጋቸውን ባጠናከሩባቸው በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች በአማዛኙ ከራሳቸው ሜዳ ከፍ ብለው የተለመደውን የመጨረሻ ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር ይጣሩ እንጂ ነጥባቸውን ከፍ አድርገው ወድድር አመቱን በድል ለመጨረስ ውጤቱን ለማስጠበቅ ሜዳቸው ላይ ያዘወትሩ የነበሩትን የአዞዎቹን ተከላካይ መስመር አልፈው ግልፅ የግብ ማጋባት ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ እያስተዋልን ጨዋታው ወደ መገባደጀው ተቀርቧል። በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲገቡ የነበሩት አዞዎቹ 82ኛው ደቂቃ ላይ አህመድ ሁሴን ከግብ ጠባቂው በንክኪ አልፎ ክፍት ግብ ላይ ኳሱን ደርሶ መቆጣጠር አቅጦት ያመለጣቸው አስቆጪው አጋጣሚ ይጠቀሳል።
እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጥሩ ፉክክር እያስመለከተ በቀጠለው በምሽቱ ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕናዎች የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ጠንከር ብለው ጫና ቢያደርጉም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው የአዞዎቹን ተከላካዮች አልፈው ግብ ማስቆጠር ተስኗቸው አዞዎቹ በአንፃራዊነት ልዩነት ፈጣሪ የነበረችውን የቡታቃ ሸመናን ቅጣት ምት ግብ አስጠብቀው ለመውጣት በሙሉ ሀይላቸው እየተከላከሉ በመጨረሻም ተሳክቶላለው በቡታቃ ሸመና ብቸኛ ግብ የውድድር አመቱን በድል እንዲሁም ደረጃቸውን አሻሽለው አመቱን ቋጭተዋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየት የአርባምንጭ ከተማው አሰልጣኝ በረከት ደሙ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ በተመለሱበት እና ከባድ በሆነው በዘንድሮ ፉክክር ላይ ከነባር ቡድኖች የተሻለ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቅ መቻላቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን አንስተው እንደአሰልጣኝ እራሳቸውን ማሳደግ፣ መሻሻል እና የተሻለ ደረጃ የመድረስ እቅድ እንዳላቸው ገልፀዋል። የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በሰጡት አስተያየት የግብ አጋጣሚ ፈጥረው ማምከናቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው እና አዲስ የገቡ ተጫዋቾ ያሳዩት ነገር ጥሩ እንደሆነ ተናግረው በቡድኑ ላይ የጥራት ችግር አለ እሱን በስራ እናርማለን የሚል አስያየት ሰጥተዋል።